“በቁጥጥር ስር የዋልኩት በአልፋሸር አየር ማረፊያ አቅራቢያ ነው፡፡ ልክ እንደያዙኝ ወደ አንድ ሆስፒታል አስገቡኝ፡፡ ከዚያም ወደ ኮማንደሩ ቤት አዛወሩንና ለአንድ ሣምንት ቆየን፡፡ በምርኮ በቆየሁባቸው ቀናት ወታደሮች በመርፌ ደሜን እየቀዱ ወስደውታል። ምን ያህል እንደወሰዱ አላውቅም፤ ብዙ ነው፡፡ ‘ሁሉንም ወስደውብኝ ልሞት ይሆን እንዴ?’ ብዬ ሥጋት ገብቶኝ ነበር። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ለማምለጥ የምችልበት አማራጭ አልነበረኝም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ዓይኔን በጨርቅ ሸፍነውት ምንም ማየት አልችልም ነበር፡፡ ፊት ለፊቴ የጦር መሣሪያ አንግተው ማንንም ሰው ለመግደል በተጠንቀቅ የቆሙ ወታደሮች በመኖራቸውም ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡”
ይህን የሚለው አደም ነው፡፡ ሱዳናዊው አደም የአልፋሸር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በርግጥ አደም ትክክለኛ ሥሙ ሌላ ነው፡፡ ለደኅንነቱ በመፍራቱ ነው የሚድል ኢስት ዐይ ጋዜጠኞች እንዲጠቀሙበት ይህን ተለዋጭ መጠሪያ ለራሱ የሰጠው፡፡ ያም ሆነ ይህ እውነቱ የእነ አደም ሱዳን፤ አሁንም በማያባራ ቀውስ ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፡፡ ባለፉት ሣምንታትም ወታደሮች በዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ መልኩን እየለዋወጠ ፈተናው ቀጥሏል፡፡
በዚህ ዙር የሰቆቃው ማደሪያ ባለተራው አልፋሽር ሆናለች፡፡ በምዕራብ ሱዳን ውስጥ የምትገኘው ከተማ፤ የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ነች፡፡ በታሪክ የምትነሳው በሲራራ ንግድ መናኸሪያነት ነው፡፡ የንግድ መናኸሪያነቷ በዙሪያዋ ላሉት አካባቢዎች ለሚመረቱ እህሎች እና ፍራፍሬዎች የግብርና ግብይት ማእከል አድርጓታል፡፡
አልፋሸር የሚገኝበት የዳርፉር ግዛት በታሪክ ነፃ የሆነ እስላማዊ ሡልጣኔት የነበረው ነው፡፡ እ.አ.አ ከ1596 እስከ 1637 ዳርፉርን በመራው የመጀመርያው ሡልጣን ሱለይማን ሶሎንግ አማካይነት እስልምና የመንግሥት ኦፊሴላዊ ሃይማኖት ሆኖ ታውጇል። ግዛቱን ያስተዳደሩ ሡልጣኖቹ የእስልምናን ትምህርት በማስፋፋትና መስጂዶችን በመገንባት በርካታ ሰዎች ወደ እስልምና እንዲመለሱ አድርገዋል። ግዛቱ በቅስቲቱ መካ የሚገኘውን የካዕባን ልብስ (ኪስዋ) ለዘመናት ሲያበጃጁ የነበሩ የዕደ ጥበብ ባለሞያዎች መኖሪያም ነበር፡፡
በካርቱም በሚገኘው ማእከላዊ መንግሥት መተዳደር የጀመረው በቅኝ ግዛት ዘመን እንግሊዞች የዳርፉርን ሡልጣኔት በ1916 ወደ ሱዳን ካካተቱ በኋላ ነው፡፡ ይህ የአስተዳደር ለውጥ መሠረታቸውን በናይል ላይ ላደረጉ ሕዳጣን ልሒቃን አቅም በመስጠቱ፤ ዳርፉርን ጨምሮ ሌሎችንም የዳር ሀገር ሕዝቦች ወደ ጎን ገፍቷል ይባላል፡፡
በ2015 ሚያዝያ በተጀመረው በሌተናል ጀነራል ዓብዱልፈታህ አልቡርሃን የሱዳን መደበኛ ጦርና በጄነራል ሙሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚደረገው ጦርነት ባለፉት ሣምንታት ሰፊ ውድመት ያደረሰው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ ከ550 ቀናት በላይ በከበባ የቆየችው አል ፋሸርን በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ፤ መደበኛ ትምህርትን ከስድስተኛ ክፍል በላይ ስለመዝለቃቸው ሠነድ አይገኝላቸውም የሚባሉት የሔሜቲ ወታደሮች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎችን መግደላቸውን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ እንደ አደም ያሉ ሱዳናዊያንም በድንገት ታግተው ደማቸው ያለፈቃዳቸው የተቀዳውም በእነዚሁ ወታደሮች ነው፡፡

በርግጥ የሔሜቲ ወታደሮች በአልፋሸር ጥፋት ማድረሳቸው ሲነገር ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ጥር ወር በከተማዋ ውስጥ የሚገኘውን የመጨረሻውን የዳርፉር ሡልጣን፤ የዓሊ ዲናርን ቤተመንግሥትና ሙዝየም አፈራርሰዋል፡፡ በወቅቱ ይህን የተመለከቱ በርካታ ታዛቢዎች ድርጊቱ የሀገሪቱን ግጭት አባባሽ ሊሆን ይችላል በሚል ሥጋታቸውን ሲያጋሩ ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው የፈሩት ነው፡፡ ታዛቢዎች ለዚህ መከራከሪያ ያደረጉት ጥቃቱ የተከመረ ድንጋይን የማፍረስ ብቻ ሳይሆን የሱዳንንና ሕዝቧን ባህላዊ እና ታሪካዊ ማንነት መዳፈር ነው በማለት ነበር፡፡ ቤተ መንግሥቱና ያቀፈው ሙዝየም ለፈረሰባቸው የአል ፋሸር አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ ማኅበረሰቦችን አንድ የሚያደርገውን ትዕምርት የማዳከም ሙከራ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በሱዳን ጦርነት በሁለት ጎራ እየተዋጉ የሚገኙት ሁለቱ ጀነራሎች ከዚህ ቀደም በሱዳን ታሪክ ውስጥ በርካታ ወንጀል ተፈጽሞበታል በሚባለው በዳርፉር ጦርነት ወቅት በአንድ ወገን የተሰለፉ ስለሆኑ በሚገባ ይተዋወቃሉ፡፡ ስለዚህ የትኛው የዜጎች ስል ሲነካ ይበልጥ እንደሚያሳምም ያውቃሉ፡፡ በአልፋሽርም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የተፈጸምውና የሚፍፈመውም በዚሁ መነሻ ሳይሆን አይቀርም ይባላል፡፡
የቀድሞው የዳርፉር ገዥና አማፂ አዛዥ የነበሩት ሚኒ ሚናዊ በዚህ ሣምንት ለመገናኝ ብዙኃን እንደገለጹት፣ የሔሜቲ ጦር በጥቅምት ወር መጨረሻ በአልፋሸር በሦስት ቀናት ውስጥ ቢያንስ 27 ሺሕ ሰዎችን ገድሏል። ያለፈቃዳቸው ደማቸውን ሲቀዱ የነበሩት ከዚህ የተረፉትን ጭምር ነው፡፡ ይህን ድርጊት ሚድል ኢስት ዐይ ከዐይን እማኞች፣ ከረድኤት ሠተኞች፣ ከዲፕሎማቲክ ምንጮችና ከራሳቸው ከተጎጂዎች አረጋግጫልሁ ብሏል፡፡ ወታደሮች ደሙን ቀድተውት በመንገድ ላይ በተደጋጋሚ ራሱን መሳቱን የተናገረውን አደምንና ሌሎችም የከተማው ሰዎች አሁን እንደምንም አልፋሸር አምልጠው የተጠለሉት በምዕራብ አቅጣጭ በኩል በምትገኘው ጠዊላ ነው፡፡ ጠዊላ በአሁኑ ሰአት 650 ሺሕ ተፈናቃዮችን አስጠልላለች፡፡ ከ300 በላይ የተላያዩ ሀገሮች የረድኤት ሠራተኞም በዚያ ይገኛሉ፡፡
ለበርካታ ዓመታት በዳርፉር ያገለገለ አንድ የሱዳን የረድኤት ሠራተኛ እንደገለጸው፣ ብዙ ወጣቶች ደም ስለተወስደባቸው ሲሰቃዩ ተመልክቷል። ድርጊቱን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወታደሮች “እጅግ አረመኔያዊ ድርጊቶች አንዱ ነው” ብሎታል፡፡ ክፉ ደጉን የማይለዩ ሕጻናትም ከአልፋሸር ወደ ጠዊላ ተሰደው እየተንከራተቱ ነው፡፡ ከሕፃናቱ መካከል አብዛኞቹ ከወላጅ ጋር የተጠፋፉ ናቸው፡፡ አልጀዚራ የኖርዌይጂያን ሬፍዩጂ ካውንስልን መረጃ ጠቅሶ ሐሙስ እለት እንደዘገበው፤ የተጠፋፉት ሕጻናት ቁጥር ቢያንስ 400 ደርሷል፡፡

ድርጅቱ እንዳለው፤ ብዙዎች ሕፃናት ከአልፋሸር በሽሽት ወቅት ከወላጆቻቸው ተለያይተዋል፣ ሌሎች ደግሞ ወላጆቻቸው ጠፍተዋል፣ ታስረዋል አልያም ተገድለዋል።
ይህ ሁሉ ጥፋት በእጃቸው ከደረሰው ከሁለቱ ጀነራሎች ውስጥ፤ የዳጋሎ ጦር በሽምቅ ውጊያ የተካነ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ በአውደ ውጊያዎች ባሕርይ እየቀያየረ ሊዋጋ የሚችል ሠራዊት አላቸው ይባላል። ይህ ባሕርይ በከተማ በሚደረጉት ውጊያዎች የበላይነት እንዲይዙ ሳያስችላቸው አልቀረም፡፡ በተቃራኒው በዓብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሀገሪቱ ጦር ደግሞ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በላይ የጦር መሣሪያ አቅርቦት አለው። ታንኮች፣ ከባድ ጦር መሣሪያዎች እና የአየር ላይ የበላይነት ያለው በአልቡርሃን እጅ ነው። በዚህ ምክንያት ጦርነቱን ከሁለት የእርስ በርስ ውጊያ በኋላም በኃይል ማሸነፍ እንደሚችሉ የሚያምኑት ሁለቱ የሱዳን ጀነራሎች፤ የድርድር ጥያቄዎችን አሁንም እንደገፉ አሉ፡፡ የገፉት ሰሞነኛውን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን እንቅስቃሴ ጭምር ነው፡፡ በርግጥ በሁለቱም ጀነራሎች ጎራ የተሰለፉ በርካታ ሀገሮች መኖራቸውም ተደጋግሞ ሲነገር የሰነበተ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መሃል ሱዳናዊያንም ሰቆቃ መቁጠር እጣቸው ሆኖ ቀጥሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)
(ለዚህ ጥንቅርሱዳን ትሪብዩን እና ቢቢሲ በተጨማሪ ምንጭነት ጥቅም ላይ ውሏል)












