Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየጉርምስና ጊዜ እስከ 32 ዓመት ዕድሜ ድረስ ሊዘልቅ ይችላል - አዲስ የጥናት...

የጉርምስና ጊዜ እስከ 32 ዓመት ዕድሜ ድረስ ሊዘልቅ ይችላል – አዲስ የጥናት ግኝት

“ኔቸር ኮሚኒኬሽን” በተሰኘ ጆርናል ላይ የታተመ አዲስ የጥናት ግኝት፤ ቀድሞ ከ20 ዓመት ፈቅ ላይል ይችላል የሚባለውን የጉርምስና እድሜ እስከ 32 ድረስ ሊዘልቅ ይችላል ሲል አመልክቷል፡፡ በጥናቱ ላይ የተሣተፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ አራት የዕድሜ አርከኖች ማለትም እስከ ዘጠኝ፣ ከዘጠኝ እስከ 32፣ ከ32 እስከ 66 እና ከ66  እስከ 83 ድረስ ባለው በአንጎል እድገት በጣም ወሳኝ ለውጥ ይከሰታል፡፡ እድሜያቸው እስከ 90 ውስጥ የሚገኝ አራት ሺሕ ሰዎችን ያሳተፈው ጥናት፤ የሰው ልጅ በአምስት የአንጎል እድገት ደረጃ እንደሚያልፍ ይገልጻል፡፡

የመጀመርያው ምዕራፍ ከውልደት ጀምሮ ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ይህ “የልጅነት ጊዜ” በሚለው ምድብ የተካተተ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አንጎል ፈጣን መዋቅራዊ ለውጥ ያካሄዳል፡፡ መረጃን በማዋሐድ ትርጉም የሚሰጠው የአንጎል ክፍል ማለትም ግራጫው (Grey matter)ና ወደ ሌሎች የነርቭ ክፍሎች የሚያስተላልፈው ነጩ ክፍል (White matter) በፍጥነት ያድጋል። ይህ እድሜ ወደ ጉርምስና ሽግግር የሚደረግበት፣ የሆርሞንና ኒውሮሎጂካል ለውጦችም የሚስተዋሉበት ነው፡፡ በዚህ ምእራፍ ማጠናቀቂያ ሴት ልጅ ወደ ኮረዳነት ልትሻገር የምትችለው ከስምንት እስከ 13 ዓመት ባለው ውስጥ ነው፡፡ ወንዶች ደግሞ ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት ድረስ ለውጦችን ያስተናግዳሉ፡፡

ወደ ጉርምስና ሽግግር የሚደረገው በሁለተኛው ምዕራፍ ነው፡፡ ተማራማሪዎች ይህን ከዘጠኝ እስከ 32 ዓመት ባሉት እድሜ ክልል ውስጥ አካተውታል፡፡ በዚህ ምዕራፍ የአንጎል አውታሮች ብስለት በማሳየት ይበልጥ እየተቀናጁ ይሄዳሉ፡፡ አስቀድሞ የወጡ ጥናቶች ጉርምስና ቢበዛ እስከ 20 ዓመት ብቻ ሊቆይ እንደሚችል ቢያመለክቱም አዲሱ ጥናት ይህን ይሽራል፡፡

ጥናቱ የሰው ልጅ ከጉርምስና ወደ አዋቂነት (Adulthood) የሚያደርገው ሽግግር ተፈጥሮአዊ መሠረት ባለው የአካል እድገት ላይ የተመሠረተ ብቻ ሳይሆን፤ በባሕል፣ በታሪክ እንዲሁም ማኅበራዊ ተጽእኖዎች ላይ ሊመርኮዝ እንደሚችል ያትታል፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው አካሉ ቢደነድንም በአዋቂነት ምድብ ውስጥ ሳይገባ እድሜው 32 እስኪደርስ በጉርምስና ማእቀፍ ውስጥ ሊቆይ ይችላል፡፡

አጥኚዎቹ ሦስተኛውን ምዕራፍ የአዋቂነት ጊዜ (Adulthood) ሲሉ ሠይመውታል፡፡ ከ32 እስከ 66 ያሉትን ዓመታት ያካተተው ይህ ምዕራፍ፤ ከቀደሙት ሁለቱ በአንጻራዊነት አንጎል እድገቱ የሚገታበትና ምንም ዐይነት ለውጥ የማያስመዘግብበት እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።

የቅድመ እርጅና በሚል የተሰየመው አራተኛ ምዕራፍ፤ ከ66 እስከ 83 ያሉትን እድሜዎች ያቅፋል፡፡ ከ83 በላይ እድሜን የሚያቅፈው አምስተኛው ምዕራፍ ደግሞ እንደሌሎቹ “በቂ አስረጂ ናሙና ባይገኝለትም” የአንጎል እድገት እየቀነሰ የሚሄድበት በሚል ተፍርጇል፡፡ የዚህ ጥናት ናሙና የተወሰደው ከእንግሊዝና አሜሪካ ዜጎች ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የጉርምስና ዕድሜ ከ10 እስከ 19 ዓመት መሆኑን ይገልጻል። በእንግሊዙ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮኢንፎርማቲክስ ፕሮፌሰርና ከጥናቱ አዘጋጆች አንዱ የሆኑት ዱንካን አስትል፤ አዲሱ ጥናት የአንጎልን ተጋላጭነት በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳ ይግዘናል ሲሉ ለኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ተናግረዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular