የሶማሊያ መንግሥት በሀገሪቱ የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ሳቢያ የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ በመምጣቱ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ርዳታ ጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) እንዳስታወቀው፤ በሀገሪቱ ሰሜን፣ በመካከለኛ እና በደቡባዊ ክልሎች ሁኔታው ተባብሷል፡፡ በዚህም በቀጣይ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሶማሊያ ዜጎች ለድርቅ አደጋ ይጋለጣሉ ሲል አስጠንቅቋል። እንዲሁም ወደ 2 ሚሊዮን ገደማ ከአምስት ዓመት በታች ሕጻናት እስከ ሐምሌ 2026 ድረስ ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ ይችላሉ ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በሀገሪቱ በድርቁ ክፉኛ ከተጋለጡት አካባቢዎች አንዷ ፑንትላንድ ነች፡፡ የአካባቢው ባለሥልጣናት ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል 130 ሺሕ ሰዎች ለሕይወት አስጊ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በዚህ ወር አጋማሽ ኦቻ እና የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በባሪ እና ኑጋል ክልሎች ባደረገው ግምገማ፤ ማኅበረሰቡ ከባድ የንጹሕ ውሃ እና የምግብ እጥረት እንደገጠመው አረጋግጧል።

በዚህም በቀጣዮቹ ወራት የነዋሪዎች ሞት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ስለ ሁኔታው የተናገሩት በባሪ ክልል በምትገኘው ሻሕዳ መንደር ከንቲባ ዓብዲገኒ ዑስማን ዑመር፤ ከባለፈው ዓመት ወዲህ ዝናብ አለማግኘታቸውን በማስታወስ፤ አሁን የተከሰተውን ድርቅ በዓመታት ውስጥ “እጅግ አስከፊው” ሲሉ ጠርተውታል፡፡ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ቤተሰቦች ከሦስት ወር በፊት ወደዚህ መጥተዋል ሌሎችም እየመጡ ነው” ያሉት ከንቲባው፤ “ወንዶቹ ግጦሽ እና ውሃ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ እያቀኑ” መሆኑንም ተናግረዋል። አክለውም መንደሩ እነሱን ለመርዳት አቅም እንደሌለው በመግለጽ ማኅበረሰቡ የውሃ እና የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል መባሉን በተመለከተ የሶማሊያ ክልል ባለሥልጣናት እስካሁን የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡
ሌላው የደንጎራዮ ወረዳ ከንቲባ ሙሐመድ ዐብዲልዓዚዝ፤ ለአራት ተከታታይ ወቅቶች ምንም አይነት ዝናብ እንዳላገኙ አስረድተዋል። ከንቲባው አያይዘውም በአካባቢ ያሉ ነዋሪዎች አርብቶ አደር በመሆናቸው በድርቅ ምክንያት ኑሯቸው አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸዋል። አክለውም ወደ 8 ሺሕ ገደማ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል። በሶማሊያ በነሐሴ ወር ሲሰጥ የነበረው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ድጋፍ በዚህ ወር ወደ 350 ሺሕ ዶላር ዝቅ ብሏል ተብሏል። ይህም ቀውሱን አሁን ካለበት የከፋ እንደሚያደርገው ሥጋታቸውን አጋርተዋል።
በ2025 የዓለም አቀፍ የረሐብ መረጃ ጠቋሚ መሰረት፤ ሶማሊያ ከ123 ሀገሮች መካከል 123ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












