Homeዜናና ወቅታዊዜናጋዛን በዐስርተ ዓመታት ውስጥ መልሶ ለመገንባት 70 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ያስፈልጋል -...

ጋዛን በዐስርተ ዓመታት ውስጥ መልሶ ለመገንባት 70 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ያስፈልጋል – የተመድ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ)፤ በቀጣዮቹ ዐሥርተ ዓመታት ጋዛን መልሶ ለመገንባት 70 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ያስታወቀው አዲስ ባወጣው ሪፖርት ነው፡፡ ሪፖርቱን ይፋ ባደረገው የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ መረጃ መሠረት፤ የእስራኤል የጦር ድብደባ ጋዛን አዘቅት ውስጥ የከተተ ነው፡፡ በዚህም እ.አ.አ በ2023/2024 ኢኮኖሚው በ87 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

በእስራኤል ላይ የሚፈጸመው የተቀናጀ ጥፋት ባስከተለው ኢኮኖሚያዊ ድቀት የፍልስጤም የነፍስ ወከፍ ገቢ 161 ዶላር በማስመዝገብ ከዓለም ዝቅተኛ ከሚባሉት ተርታ ውስጥ ተመድቧል፡፡ ሪፖርቱ በፍልስጤም የተከሰተውን ቀውስ “በዓለም ዙሪያ ከ1960 ወዲህ ከተከሰቱት አስር የከፋ የኢኮኖሚ ቀውሶች መካከል አንዱ ነው” በሚል ፍርጆታል፡፡ በጋዛ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስም “ለየት ያለና እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ የከፋ” መሆኑን ይገልጻል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደት ምክትል ልዩ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ፤ ሰኞ እለት በአካባቢው ያለው ሁኔታ አሁንም “ጨለማ” እንደሆነ ተናግረዋል። ሕዝቡ “የማይቻሉ የኑሮ ፈተናዎችን” እየተጋፈጠ በመምጣቱ፤ የሰብዐዊ ድጋፍ እንዲጨምር አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። በጋዛ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሁንም ተፈናቅለዋል ያሉ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎች ንጹሕ ውሃ፣ ምግብ እና የሕክምና እንክብካቤ ባልተሟላላቸው በመጠለያዎች ውስጥ ተፋፍገው እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አጋሮቹ አሁንም እንደ ድንኳን እና ብርድ ልብስ የመሳሰሉ መጠለያ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ከፍተኛ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው ነው ያሉት ራሚዝ አላክባሮቭ፤ የክረምት ወራት እየተቃረቡ ሲሄዱ እነዚህ መዘግየቶች በአስቸኳይ መፍትሔ ማግኘት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

አክለውም ሆስፒታሎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅርቦት ሳይኖራቸው ታካሚዎችን ለማዳን ትግል ውስጥ እንደሚገኙ በመግለጽ፤ የርዳታ አቅርቦት እንዲጨምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የጋዛ የመገናኛ ብዙኃን ቢሮ እስራኤል በቀን 200 የርዳታ ተሽከርካሪዎችን ብቻ መፍቀዷን አስታውቋል፡፡ ይህ መጠን በተኩስ አቁሙ ስምምነት ከተፈረመው በ600 ያንሳል፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንዳመለከተው፤ አብዛኛዎቹ የጋዛ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን መግዛት አይችሉም። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular