በጋዛ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ቀደም ሲል ከታሰበው በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ሣምንታዊው የጀርመን ጋዜጣ “ሳይት” የሀገሪቱን የምርምር ተቋም አዲስ ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በሰሜን ምሥራቃዊዋ የወደብ ከተማ ሮስቶክ ውስጥ በሚገኘው ታዋቂው የማክስ ፕላንክ የዲሞግራፊክ ጥናት ተቋም የምርምር ቡድን ሥሌት መሠረት፤ ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ቢያንስ 100 ሺሕ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተባባሪ መሪ ኢሬና ቼን ሲናገሩ፦ “[በጥናቱ] የሟቾቹን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ባንችልም፤ በተቻለ መጠን ትክክለኛ የሆነውን ቁጥር ግምታዊ ስሌት ለማስቀመጥ እየሞከርን ነው” ብለዋል።
በዚህም በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ከ99 ሺሕ 997 እስከ 125 ሺሕ 915 ሰዎች ሞተዋል አልያም ተገድለዋል። ተመራማሪዎቹ ያስቀመጡት አማካይ የሟቾቹ ቁጥር ግምት ደግሞ 112 ሺሕ 69 ነው፡፡
የማክስ ፕላንክ አጥኚዎች ከተለያዩ ምንጮች የተገኘውን መረጃ አሰባስበው ይፋ ላደረጉት ስታቲስቲካዊ ትንበያ፤ የሟቾቹን ቁጥር ለማወቅ በጋዛ ከሚገኘው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ በተጨማሪ ገለልተኛ የሆኑ አጥኚዎችንና በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የተጋሩ የሞት ሪፖርቶችን አካትተዋል።
በፍልስጤም የጋዛን የሟቾች በተመለከተ ቁጥር እስካሁን ድረስ በብቸኛነት ኦፊሴላዊ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡ በሚኒስቴሩ ይፋዊ መረጃ፤ በጦርነቱ የመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ 67 ሺሕ 173 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የተለያዩ የምርምር ቡድኖች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቆጠራ ውስንነት እንዳለበት ይገልጻሉ። ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ወቅት በርካታ ሆስፒታሎች መደበኛ ሥራቸውን ለማቆም ስለተገደዱ በአሁን ሰዐት ከሟች ዘመዶች የሚመጡ የሞት ሪፖርቶችን ባቋቋመው አጣሪ ቡድን ከተረጋገጠ በኋላ ጀምሯል፡፡ አስቀድሞ በቆጠራው የሚያካትተው ግን ከሆስፒታል የሞት ምስክር ወረቀት ያላቸውን ብቻ ነበር። ነገር ግን በቦምብ ድብደባ የፈራረሱ ሕንፃዎች ሥር የተደበቁ አስከሬኖች በአብዛኛው አይመዘገቡም።
በአንጻሩ ማክስ ፕላንክ የተሰኘው ቡድን ጥናቱን ያካሄደው ቀደም ባሉት ግኝቶች ላይ በመመሥረት ሌሎች ዝርዝሮችን በማከል መሆኑ ተገልጿል፡፡ የወንዶችና የሴቶች እንዲሁም የተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ለየብቻ ተፈትሿል፡፡ ይህ አቀራረብ ይበልጥ ትክክለኛ አጠቃላይ አኃዞችን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ማን እንደሞተ በዝርዝር ለመለየት ያስችላል ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ ይፋ ባደረጉት ሥሌት መሠረት፤ 27 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የጦርነቱ ሰለባዎች እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ሲሆኑ፤ 24 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው። አጥኚዎቹ በጋዛ ቀጠና ጦርነት ሰዎች በሕይወት የሚኖሩበት ዕድሜ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖም አስልተዋል። ከጦርነቱ በፊት በጋዛ በአማካይ በሕይወት የሚቆዩበት እድሜ ለሴቶች 77 ዓመት፤ ለወንዶች ደግሞ 74 ዓመት ነበር። ጦርነቱ በተነሳበት በ2024 የሴቶች ዕድሜ 46፣ የወንዶች ዕድሜ ደግሞ 36 እንደሚሆን የሕዝብ ቆጠራ ባለሙያዎች ግምት አስቀምጠዋል። (ሚንበር ቲቪ)












