የአሜሪካው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ፤ ከፈረንጆች አዲስ ዓመት በፊት የአውስትራሊያ መንግሥት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ያጸደቀውን ሕግ፤ በሚስተዳደራቸው ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የአውስትራሊያ መንግሥት ከታኅሣሥ ጀምሮ ተፈጻሚ የሚያደርገውን ይህን ሕግ ያጸደቀው፤ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ነበር። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ዕድሜ የሚያረጋግጠውን አሠራር መዘርጋት ያስፈለገው ታዳጊዎች “ከእውናዊው ዓለም እየተነጠሉ” በመሆኑ ነው ብለው ነበር፡፡ መድረኩ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ የገለጹት አንቶኒ አልባኒዝ፤ የሚዲያ አማራጩ ሕጻናትን ከእውናዊው ዓለም ከማቆራረጡ በተጨማሪ “ከእውነተኛ ጓደኞቻቸው ጭምር እያራቀ” እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በማኅበራዊ ሚዲያ ምክንያት ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውንም ተናግረው ነበር፡፡
ሀገሪቱ ይህን ሕግ ተፈጻሚ በማያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ላይ እስከ 32 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ደንግጋለች፡፡

የቴክኖሎጂ ኩባንያው ለታዳጊ ተጠቃሚዎች በላከው ማሳወቂያ ከታኅሣሥ 4 ጀምሮ ፌስቡክና ኢንስታግራም መጠቀም እንደማይችሉ በመግለጽ፤ አካውንታቸውም ለእነርሱም ሆነ ለሌላ ሰው እንደይታይ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡ ለመጠቀም ሙከራ የሚያደርግ ካለም አካውንቱ እንደሚታገድ ማስጠንቀቂያ ልኳል። ሜታ “16 ዓመት ሲሞላቸው እንደገና መጠቀም እንዲችሉ” የማሳወቂያ መልእክት እንደሚልክ ጠቁሟል፡፡
ከፌስቡክና ኢንስታግራም በተጨማሪ የአውስትራሊያ መንግሥት እንደ ቲክቶክ፣ ዩትዩብ፣ ኤክስ፣ ስናፕቻት እንዲሁም ሌሎች የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያዎች ላይ እግዱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጿል።
ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማቀብ እድሜን የሚያረጋግጥ አሠራር በዘረጋችው አውስትራሊያ፤ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ያሉ ከ350 ሺሕ በላይ የኢንስታግራምና ከ150 ሺሕ በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ሀገሪቱ በሕዝብ ትምሕርት ቤቶች ተማሪዎች ‘ስማርት’ ስልኮችን እንዳይጠቀሙ እገዳ ከጣለች ሁለት ዓመት ተቆጥሯል፡፡
የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስበው “ዩጎቭ” ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት፤ 61 በመቶ አውስትራሊያዊያን ከ17 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ እቀባ እንዲጣልባቸው ፍላጎት አላቸው፡፡ ሆኖም አንዳንድ በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚሠሩ ተመራማሪዎች ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ሙሉ ለሙሉ ማቀብ ተዘዋዋሪ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












