የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም፤ ለሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 9/2018 አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ወደ መዲናዋ ሲዘልቁ የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል አድርግውላቸዋል፡፡ ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ባሠፈሩት ጽሑፍ፤ “ጉብኝትዎ በማሌዢያ እና ኢትዮጵያ መካከል እያደገ ያለውን ወዳጅነት እና ትብብር የሚያሳይ[]፤ በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ውስጥም በጠቃሚ ጊዜ የተደረገ ነው” ብለዋል፡፡
ለአንዋር ኢብራሂም ደማቅ አቀባበል ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከአንድ ዐመት በፊት በጥቅምት 2017 ወደ ኳላላምፑር ተጉዘው ተመሣሣይ አቀባበል አስተናግደዋል፡፡

የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝቱን በማስመልከት ባሠራጨው መረጃ እንዳመለከተው፤ አዲስ አበባ ውስጥ የማሌዢያ ኤምባሲ እንደገና መከፈቱን ተከትሎ የተከናወነው ጉብኝት፤ እ.አ.አ በጥር 1965 ከተጀመረው የኢትዮጵያ እና የማሌዥያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጅማሮ 60ኛ ዓመት ጋር ተገጣጥሟል፡፡ ይህም “ማሌዥያ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው” ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ የጠቀሰው የማሌዢያ ኤምባሲ ከ43 ዓመት በኋላ እንደገና በአዲስ አበባ የተከፈተው መስከረም 13/2018 ነው፡፡ ኤምባሲው በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት ሥራውን እያከናወነ ያለው በሸራተን አዲስ ሆቴል ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ነው፡፡
የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ሲደርሱ የፓርላማ አባላትን፣ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የንግዱ ማኅበረሰብ ልዑካንን አስከትለዋል፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ አባላት ያስከተሉት በማሌዥያ-ኢትዮጵያ ከፍተኛ የንግድ ፎረም ላይ እንዲሳተፉ ነው፡፡
በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በግብርና እና በሸቀጦች፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ትብብርን ይበልጥ ለማጠናከር አዳዲስ መንገዶችን በመቀየስ ዙርያ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በተለይም በአሲያን እና በአፍሪካ አህጉር ላይ በተከሰቱ አዳዲስ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።

ከዚህ በማስከተል ሁለቱ መሪዎች በቱሪዝም እና በጤና መስክ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚፈረመው ስምምነት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኳላላምፑር ከተማ ምክር ቤት መካከል የትብብር ሰነድ ፊርማ ሥነ ሥርዐት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ዓመት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አሕጉር የማሌዥያ 26ኛ ትልቋ የንግድ አጋር ነች፡፡
ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚመሯት ማሌዢያ፤ እስልምና ይፋዊ ሃይማኖት ሆኖ ያገለግላል፡፡ የሸሪዓ ሕግ በቤተሰብ እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አለው። የማሌዥያ ሙስሊም ሕዝብ ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት 63 ነጥብ 5 በመቶ ገደማ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












