የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛ እና ፍልስጤማዊያንን በሚመለከት ያቀረቡትን ረቂቅ ውሳኔ ሰኞ ዕለት አጽድቋል፡፡ አምስት ቋሚ አባላት እና ዐሥር ተለዋዋጭ አባላት ባሉት ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ 13 ሰዎች ሀገሮች ድጋፍ ሲሰጡት፤ ሩሲያ እና ቻይና በድምጸ ተዐቅቦ አልፈውታል፡፡
እስራኤል በስብሰባው ላይ እንድትገኝ ቢፈቀድላትም ድምጽ መስጠት ግን አልቻለችም፡፡ በተጨማሪም በስብሰባው ላይ በመጨረሻ ደቂቃ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ስለ ፍልስጤም ሀገረ መንግሥት የሰፈረው አገላለጽ እንዲወጣ ግፊት ብታሳድርም ሳይሳካ መቅረቱን የሚድል ኢስት ዐይ ዘገባ ያመለክታል፡፡
አሜሪካ ስለ ፍልስጤም መንግሥትነት በሰነዱ ላይ የቀረበውን አገላለጽ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጓ፤ የትራምፕ አስተዳደር ከእስራኤል ተቃውሞ ባሻገር ከቁልፍ ሙስሊም አጋሮቹ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ለማስቀጠል አቁም መያዙን ጠቋሚ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በመጀመሪያ ሰነዱ ሲዘጋጅ አሜሪካ የፍልስጤምን ራስን በራስ የመወሰን መብት ሳታካትት ቀርታ የነበረ ቢሆንም ሙስሊም እና ዐረብ ሀገሮችን ለማረጋጋት ለውጡ እንዲካተት ተድርጓል፡፡ በምክር ቤቱ የጸደቀው ውሳኔ፤ የፍልስጤም አስተዳደር ማሻሻያ ካደረገና የጋዛ መልሶ ማልማት ከተረጋገጠ፤ የፍልስጤም ራስን በራስ የመወሰን እና ወደ ሀገርነት የሚወስደውን ጥርጊያ መንገድ የሚያደላድል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል አስፍሯል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ውሳኔው “በጋዛ ቀጠና ውስጥ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ለማስፈን፣ የሰብአዊ ርዳታዎችን ያለ እንቅፋት ለማቅረብ እንዲሁም የፍልስጤምን ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና ሉዐላዊ መንግሥት የመመሥረት መብት” ማረጋገጫ ነው ብሏል። በተጨማሪም “የፍልስጤም መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት የፍልስጤምን ወረራ ለማስቆም እና ነፃነትን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ፍቃደኝነታቸውን ላሳዩ” ሁሉም ሀገሮች አድናቆቱን ገልጿል፡፡
ይህ ውሳኔ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለፍልስጤም እውቅና የሰጡ በርካታ ምዕራባውያን ሀገሮች ላይ ርምጃ ባለመውሰዳቸው በተቃዋሚዎቻቸው ትችት የበረታባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፈው እሑድ ለካቢኔያቸው የፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ሐሳብ አሁንም እንደሚቃወሙ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ጽንፈኛ ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአሜሪካ የቀረበውን ስለ ፍልስጤም ግዛት ያሰፈረው የውሳኔ ሐሳብየሚጸድቅ ከሆነ፤ የፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣናት መገደል አለባቸው በማለት ዛቻ ሰንዝረው ነበር፡፡ በወቅቱ መግለጫውን የተቸው የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በፍጥነት ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሜሪካ በቀረበው እቅድ መሠረት፤ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ግንኙነት የሌለው “ቴክኖክራቲክ” የፍልስጤም አመራር የጋዛን አስተዳደር ይረከባል። ይህ የፍልስጤም አመራር የሚመረጠው የሰላም እቅዱን ተግባራዊነት በሚቆጣጠር አዲስ ዓለም አቀፍ አካል ነው። ትራምፕ “የሰላም ቦርድ” ሲሉ የጠሩት ይህ አካል፤ ስምምነቱ እንዲሳካ የማድረግና ቁልፍ የቀጣናው እንዲሁም ዓለም አቀፍ መሪዎችን የማሰባሰብ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ተናግረዋል። የቁጥጥር አካሉ ሊቀመንበር ራሳቸው እንደሚሆኑም ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












