Homeዜናና ወቅታዊዜናበመዲና አቅራቢያ የዑምራ ተጓዦችን የጫነ አውቶቡስ ከነዳጅ ቦቴ ጋር በመጋጨቱ የ45 ሕንዳውያን...

በመዲና አቅራቢያ የዑምራ ተጓዦችን የጫነ አውቶቡስ ከነዳጅ ቦቴ ጋር በመጋጨቱ የ45 ሕንዳውያን ምእመናን ሕይወት አለፈ

ሕንዳውያን የዑምራ ተጓዦችን የያዘ አውቶቡስ ሳዑዲ ዐረቢያ መዲና ከተማ አቅራቢያ ነዳጅ ከጫነ ቦቴ ጋር በመጋጨት 45 መንገደኞች ሕይወት ሲያልፍ፤ አንድ ብቻ በሕይወት መትረፉ ተሰምቷል፡፡ አደጋው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምእመናን ላይ የደረሰ እጅግ አስከፊ የተሽከርካሪ አደጋ ነው ተብሏል።

የሕንድ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፤ በአውቶቡሱ ውስጥ 46 ምእመናን ተሳፍረው ነበር፡፡ በአብዛኛው ከሃይድራባድ የተነሱት በርካታ ምእመናን ያሳፈረው አውቶቡስ ነዳጅ ከጫነው ተሽከርካሪ ጋር የተላተመው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነው፡፡ ሕይወታቸው ካለፉት ውስጥ በብቸኝነት የተረፈው ምእመን በሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡

ምእመናኑ አደጋው የደረሰባችው ከመካ የዑምራ ሥነ ሥርዐቱን ፈጽመው ወደ መዲና ሲመለሱ ነው፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ የነፍስ አድን ቡድኖች ከነዳጅ ማጓጓዣው ጋር ግጭት ከተከሰተ በኋላ አውቶቡሱ በእሳት ነበልባል ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ይህም የተጎጂዎችን ማንነት ለመለየት አዳጋች አድርጓል፡፡

ይህን ተከትሎ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኤክስ ላይ ባሠፈሩት ጽሑፍ፤ በደረሰው አደጋ በጥልቅ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪያድ የሚገኘው ኤምባሲ እና በጅዳ የሚገኘው ቆንስላችን የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

በሕንድ ፓርላማ የሃይደርባድ ተወካይ አሳዱዲን ኦዋይዝ ኤ ኤን አይ ለተሰኘ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ የሟቾቹን አስከሬን ወደ ሕንድ ለማስመለስ የፌዴራል መንግሥቱን ርዳታ ጠይቀዋል፡፡ ተወካዩ በሰጡት መረጃ መሠረት፤ 54 ሰዎች ከሃይድራባድ ወደ ጂዳ ለዑምራ በረራ ያደረጉት ጥቅምት 30/2018 ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ሰዎች በመካ ሲቆዩ፤ አራቱ ደግሞ በሌላ ተሽከርካሪ ወደ መዲና መሄድ መርጠዋል። የተቀሩት 46 ሰዎች አደጋውን ባስተናገደው አውቶቡስ ተጉዘዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular