Homeዜናና ወቅታዊዜናየትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሐማስ ዋና ተደራዳሪ ኸሊል አል ሐያ ጋር...

የትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሐማስ ዋና ተደራዳሪ ኸሊል አል ሐያ ጋር ሊገናኙ ነው

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ፤ ከሐማስ ዋና ተደራዳሪ ኸሊል አል ሐያ ጋር በድጋሚ ፊት ለፊት ሊገናኙ መሆኑን ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሁለት ምንጮች ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡

ልዩ ልዑኩ ከሐማስ መሪ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር እቅድ መያዛቸው ቡድኑን ከውጭ አሸባሪ ድርጅት ጎራ ለመደበችው አሜሪካ እምብዛም ያለተለመደ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ዊትኮፍ እና አል ሐያ ቀጠሮ የያዙት አሜሪካ ከሐማስ ጋር ግንኙነት መጀመሯ ለቡድኑ “ተገቢ ያልሆነ ሕጋዊነት ይሰጣል” በሚል በእስራኤልና በአሜሪካ በኩል ባሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ትችት እየተሰነዘረ ባለበት ወቅት ነው፡፡ የግብጹ አህራም ባወጣው ዘገባ ደግሞ፤ በተለይ የእስራኤል ባለሥልጣናት ዊትኮፍ ከሐማስ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየጨመረ መምጣቱ አሳስቦናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን እንቅስቃሴው አሜሪካ እንደ ግብፅ እና ኳታር ያሉ አደራዳሪዎችን በማለፍ ከሐማስ ጋር በቀጥታ ለመደራደር የያዘችው ሰፊ ስትራቴጂካዊ እቅድ አካል ነው።

በዘ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ ሁለቱ ባለሥልጣናት የሚገናኙበት ቀን ይፋ አልተደረገም፡፡ የአሜሪካውን ልዑክ የጉዞ ዕቅዶችን የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ምናልባት “የሐሳብ ለውጥ” ሊኖር እንደሚችልም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በጉዳዩ ላይ ጋዜጣው የስቲቭ ዊትኮፍን ተወካይ፣ ሐማስም ሆነ ዋይት ሐውስ አስተያየት እንዲሰጡ ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካልኝም ብሏል፡፡

ምንጮቹ ሁለቱ ባለሥልጣናት የሚገናኙ ከሆነ የውይይት ርእስ ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ዋንኛው ጉዳይ የጋዛ ተኩስ አቁም ነው፡፡ የተኩስ አቁሙ የተፈረመው ሁለቱም ሰዎች በግብጽ ሻርም አልሸይኽ በተገናኙበት ወቅት ነው፡፡ ከፊርማው ሥነ ሥርዐት በፊት በተደረገው ውይይት ላይ የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነርም ተሳታፊ ነበር፡፡

ውይይቱን በተመለከተ ባለፈው ወር በሲቢኤስ ቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩ ስቲቭ ዊትኮፍ፤ በመስከረም የእስራኤል አየር ኃይል የሐማስ ባለሥልጣናት በኳታር ስብሰባ ላይ በነበሩበት ሚሳኤሎችን በመተኮስ የኸሊል አል ሐያን ወንድ ልጅ መግደላቸውን በማስታወስ “ያጽናህ” እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡ እ.አ.አ በ2011 ወንድ ልጃቸውን በወሰደው አደንዛዠ ዕጽ ምክንያት በሞት የተነጠቁት ዊትኮፍ፤ “ሁለታችንም ተመሳሳይ ሕመም የምንጋራ ወላጆች ነን ብዬዋለሁ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዊትኮፍ ከሐማስ ጋር የተገናኙ የመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣን አይደሉም። የሀገሪቱ የግምጃ ቤት ባለሥልጣን አዳም ቦህለር በመጋቢት ወር በኳታር ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ከቡድኑ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በወቅቱ በሐማስ ቁጥጥር ስር የነበረውን የአሜሪካ-እስራኤል ዜግነት ያለው ግለሰብ እንዲፈታ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular