የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ)፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ የተከሰተውን የሄሞራጂክ ፊቨር ሪፖርቶችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ማእከሉ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሄሞራጂክ ፊቨር መከሰቱን ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ዣን ካሴያ ከኢፌዴሪ ከጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ጋር በስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ሲዲሲ ሣምንታዊ የጤና ድንገተኛ አደጋዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፤ ዶ/ር ዣን ካሴያ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጉዳይ በማንሳት በበሽታው ምላሽ ዝግጁነት ዙርያ ለአባል ሀገሮች ገለፃ አድርገዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን በመግለጽ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ጋር መሥራቱን እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡ ተጨማሪ መረጃ ሲገኝና የላቦራቶሪ ውጤቶቹ ሲረጋገጡ ወቅታዊ መረጃዎችን ከመስጠት ባሻገር አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
ትናንት ሐሙስ በተመሳሳይ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ በኢትዮጵያ የሄሞራጂክ ፊቨር ወደተከሰተባቸው ከተሞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት የሚመሩት ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር ባንድነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከባለሞያዎች በተጨማሪ መድኃኒቶች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መላኩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፈንድ 300 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ፈቅጃለሁ ብለዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ቢሮዎች ድንበር ተሻጋሪ ሥርጭትን ለመከላከል በትብብር እየሰራ መሆኑን በመጠቆም፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ድጋፉን ለማስፋት ዝግጁ እንደሆነም አመልክተዋል።
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 3/2018 ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ እስከአሁን ድረስ ስምንት ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረዋል። ኅብረተሰቡና የሚመለከታቸዉ የባለድርሻ አካላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌላ ተጨማሪ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ፣ ለመከላከል ጥንቃቄዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስቧል። ከሚኒስቴሩ ይፋዊ መረጃ በኋላ የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሰላሙ ታደሰ “ሕክምና ሲሰጡ የነበሩ” ዶክተር እና ነርስን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን መናገራቸው በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












