የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፤ በሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በኢትዮጵያዊው ላይ ጥቃት ያደረሰው የውጭ ሀገር ዜጋ ከሥራ እንደተባረረ አስታውቋል። ድርጊቱ በተፈጸመበት በቶዮ ሶላር ኩባንያ ውስጥ ጉዳዩ የሚመለከተው የኩባንያው የሥራ ኃላፊም “ተገቢውን አስተዳደራዊ ክትትልና ርምጃ ባለመውሰዱ” ተሰናብቷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህን የገለጸው ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 4/2018 በሓዋሳ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፤ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ በሚገኘው በቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢትዮጵያዊው ሠራተኛ ላይ ጥቃት መፈጸሙን መጀመሪያ ያሳወቀው ረቡዕ ኅዳር 3/2018 ነው፡፡ በወቅቱ በተሰራጨው መረጃ፤ በዚህ ክስተት ጥቃት የተፈጸመበት ኢትዮጵያዊ የኩባንያው ሠራተኛ ተገቢው ሕክምና ተደርጎለት ወደ ቤቱ መመለሱን ገልጾ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው ሌላ መግለጫ ድርጊቱን በማውገዝ በጉዳዩ ላይ ሕግ ተላልፈው በተገኙ የድርጅቱ ሠራተኞች ላይ ተገቢውን ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዛሬው እለት እንዳለው ከሆነ፤ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ባንድነት የተፈጠረው ግጭት የማጣራት ሥራው መጠናቀቁን በመግለጽ የግጭቱ መንስኤና የተወሰደውን ርምጃ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም የግጭቱ መንስኤ “በሥራ ገበታ ላይ በተደጋጋሚ በሰአቱ አልተገኘህም” በሚል በአንድ የውጭ ዜግነት ያለው ሱፐርቫይዘርና ኢትዮዽያዊ ሠራተኛ መካከል የተፈጠረ አምቧጓሮ ነው፡፡ አለመግባባቱ መፈታት የነበረበት “የሠራተኞችን ሰብዓዊ መብት በጠበቀ መልኩ በሕግና በድርጅቱ ፓሊሲ እንጂ በፀብ መሆን እንዳልነበረበት መግባባት ላይ ተደርሷል” ያለው ኮርፖሬሽኑ፤ ርምጃው የተወሰደው የውጭ ሀገር ዜግነት ካለው ተቆጣጣሪ በተጨማሪ “ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ እንዲፈታ በወቅቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም” በተባሉ አምስት ኃላፊዎች ላይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በዘላቂነትም እንደዚህ ዐይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ሥልጠናዎች ለኩባንያው ሠራተኞችና አመራሮች በቀጣይ እንደሚሰጥም ጠቁሟል፡፡ ውሳኔውንም ቶዮ ሶላር ካምፓኒ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለት፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እንደማይታገሱ አመላካች ነው ብሏል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ዐሥር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ አንድ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ሶስት ፓርኮች የተቀናጀ መሠረተ ልማት ለባለሀብቶች እያቀረበ የሚገኝ ሀገራዊ ተቋም ነው። ድርጊቱ የተፈጸመበት ቶዮ ሶላር ለ2 ሺሕ ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ በየወሩ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት እያደረገ ያለ ድርጅት መሆኑ ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












