የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ናይጄሪያ፤ በዘንድሮ 1447 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ጉዞ ዋጋ ቅናሽ መደረጉን በብሔራዊ የሐጅ ኮሚሽን አማካይነት አስታውቃለች። የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ቦላ አሕመድ ቲኑቡ በሰጡት መመሪያ መሠረት የተደረገው ቅናሽ፤ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ተሳታፊዎች ሊገጥማቸው የሚችለውን የገንዘብ ችግር በተወሰነ መልኩ የሚቀርፍና እፎይታ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
የሑጃጅ መነሻ ሥፍራ መነሻ ያደረገው የዋጋ ቅናሽ፤ እስከ 792 ሺሕ 943 የናይጄሪያ ኔይራ (552 የአሜሪካ ዶላር) ቅናሽ የተደረገበት ነው፡፡ በዚህም ከደቡባዊ ናይጄሪያ ከሚጓዙ ሑጃጅ በዕለቱ የምንዛሪ ዋጋ ባለፈው ዓመት ከነበረው 6 ሺሕ 114 የአሜሪካ ዶላር ወደ 5 ሺሕ 562 ዝቅ ተደርጎላቸዋል። የናይጄሪያ የሐጅ ኮሚሽን ሐጅ የመፈጸም ፍላጎትና አቅም ያላቸው ምእመናን ክፍያቸውን እስከ ተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ ክፍያቸውን ማጠናቀቅ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።
የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፤ ከዚህ ቀደም ለናይጄሪያ ሰጥቶ ከነበረው 95 ሺሕ የሐጅ ኮታ፤ በተይዘው ዓመት ወደ 66 ሺሕ 910 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ተጓዦች የጤና ማረጋገጫ መስፈርቶችን እንዲያሟሉም ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉን ብሉ ፕሪንት የተሠኘ የሀገሪቱ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡
ከሐጅ ዋጋ ጋር በተገናኛ የደቡብ እስያዋ ባንግላዲሽ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የተሰጣትን 127 ሺሕ ኮታ መሙላት ባለመቻሏ፤ በዘንድሮ ዓመት የሐጅ የዋጋ ቅናሽ ማድረጓን ያሳወቀችው ከአንድ ወር በፊት ነበር። ሙስሊሞች የሚበዙባት ሀገር፤ ዝቅተኛውን የሐጅ ጉዞ ዋጋ ዋጋ 3 ሺሕ 890 ዶላር ገደማ አድርጋለች።
በኢትዮጵያም የባለፈው ዓመት የሐጅ ጠቅላላ የጉዞ ዋጋ 625 ሺሕ ብር እንደነበር አይዘነጋም። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዘንድሮ የሐጅ ስርዓትን ለማስፈጸም ከሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን በመግለጽ የሐጅ ምዝገባ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ እንደሚጀምር ያስታወቀው ጥቅምት 30/2018 ነበር፡፡ ባለፈው ዐመት አስቀድሞ ይፋ ካደረገው ዐሥር ሺሕ ምእመናን ስድስት ሺሕ ብቻ መመዝገብ የቻለው ምክር ቤቱ፤ የዘንድሮውን ዋጋ እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረገም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












