ዞሕራን ማምዲኒ የዚህ ሣምንት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን የፊት ገጽ ማልበሻ ሆኖ አለፈ።
ዞሕራን ማሸነፉን ሲያውጅ ወላጆቹን አልዘነጋም፦ “እማዬና አባዬ የእናንተ ልጅ በመሆኔ እኮራለሁ፤ እዚህ የደረስኩት በእናንተ ነው” ሲል ተደምጧል። የ34 ዓመቱ ሰው ያመሠገናቸው እናት ሚራ ናይር እና አባትዬው ማሕሙድ ማምዳኒን ነው። ከሥሙ ጋር ሥሙ በአደባባይ የሚዞረው ወላጅ አባቱ አሜሪካ ውስጥ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ መምሕር ናቸው። እናትየው ደግሞ የፊልም ባለሞያ ናቸው፤ በርካታ ሽልማት የተቀዳጁ። እናትየው ለጊዜው እዚህ ጋር ይቆዩንና ስለ አባትየው እንቀጥል።
በርግጥ ልጅዬው በፍጹም ሊዘነጋቸው የሚችል አባት አይደለም ያሉት፤ ማሕሙድ ማምዳኒ ግዙፍ ሥም ነው፡፡ ከላይ እንዳልነው ነው፤ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂ፣ ፖለቲካል ሣይንስ እና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ ምሑር፡፡ አሁን 79 ዓመት እድሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ አሜሪካ ከመጓዛቸው አስቀድሞ በካምፓላ እና ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል፡፡
ሕንድ ቦምቤይ የተወለዱት ፕሮፌሰሩ፤ በምሑራን ዓለም የሚታፈር ሥም ገንብተዋል፡፡ የአሜሪካው ፎሬን ፖሊሲ መጽሔት በ2021 ከዓለማችን 15 ሐሳብ አፍላቂዎች ጎራ መድቧቸዋል፡፡ በበርካታ ሥራዎቻቸው በፖለቲካ እና በባሕል መካከል ያለውን መስመር መርምረዋል፡፡ ከ1452 ጀምሮ የቅኝ ግዛት ንፅፅር ጥናት፣ በአፍሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የዘር ማጥፋት ታሪክ፣ የቀዝቃዛው ጦርነት፣ የፀረ ሽብር ጦርነት እና የሰብዐዊ መብቶች ሥነ መለኮታዊ ታሪክ ላይ በማተኮር በርካታ የጥናት ውጤቶችን ማበርከት ችለዋል፡፡

ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን እንደ አንድ በሞያው የታፈረ ሙስሊም ሊቅ፤ የሚወደስ ሥራ አላቸው፡፡ ይህ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተመው Good Muslim, Bad Muslim: America, the Cold War, and the Roots of Terror ይሠኛል፡፡ መጽሐፉ ወደ አንባቢያን የቀረበው ከመስከረም 2001 ክስትት ሦስት አመት በኋላ – በ2004 ነው፡፡ ይህ ወቅት ማለት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ፀረ ሽብር ዘመቻ ባሉት ጦርነት ሙስሊሞች የጥቃት ኢላማ የተደረጉበት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ማሕሙድ ማምዳኒ በዚህ ወቅት ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ጉዳዩን ከሙስሊሞች እና እስልምና ጋር ማገናኘት ትክክል አለመሆኑን በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ አሁን ምዕራባዊያን ከእስልምን እና ሙስሊሞች ጋር አቆራኝተው የሚያራግቡት ጽንፈኝነት፤ እስልምና ከሚቀዳበት ቁርአን አልያም ከሌሎች አስተምህሮችዎች የመነጨ ሳይሆን አሜሪካ ራሷ ከምታልፍበት ፖለቲካ የፈለቀ መሆኑን በማስረጃ ሞግተዋል፡፡ ማሕሙድ በመጽሐፉ “እስልምናን ከምትወቅሱ ራሳችሁን ፈትሹ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ማምዳኒ እንደሚሉት አሁን የሚታየው ሁሉ ዋንኛ መነሻው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካ ከሩስያ ጋር የገባችበት የጂኦ ፖለቲካ ፍትጊያ ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ በመጽሐፉ ሁለተኛና ሦስተኛ ምእራፎች በተለይ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በአፍጋኒስታን ምን መሣይ ነበር የሚለውን ያስቃኛሉ፡፡ የዚያን ጊዜውን የአሜሪካና የአፍጋኒስታን ሙጃሒዶችን “በፍቅር የከነፈ” ግንኙነት በ2ሺዎቹ መጀመርያ ከነበረው ሁኔታ ጋር በማገናኘት ማነፃፀሪያ አቅርበዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን/የሚፈጠረውን ጥፋት በቀላል መንገድ ከእስልምና ጋር በማገናኘት ውንጀላ የማቅረብ ባሕል መንሰራፋቱን በማንሳት የተቹት ማሕሙድ፤ ሰዎች ሲሰባሰቡ እስልምናን ከግጭት ጋር የማገናኘት አባዜ ውስጥ መውደቃቸውን ያነሳሉ፡፡ የዚህን ባሕል መንሠራፋት “ከጨቅላ አስተሳሰብ የተወለደ” እና “አደገኛ” ነው ብለውታል፡፡ በዚህ መነሻ ማንኛውንም ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር የሚስማማን ምእመና “መልካም ሙስሊም”፤ ተቃራኒ ሐሳብ የሚያራምደውን ደግሞ “መጥፎ ሙስሊም” በሚል ፍረጃ መሰጠቱንም ኮንነውታል፡፡ በዚህ ዐይነት ውንጀላ በዓለማችን ሰላም ማስፈን እንደማይቻል ተከራክረዋል፡፡
በመጽሐፉ የቀረቡት መከራከሪያዎች የምሑራንን ሠፈር የናጡ ናቸው። ከዘመናችን ዕውቅ ዓለም አቀፍ የእስልምና መምሕራን መካከል ተጠቃሸ የሆኑት ሸይኽ ያሲር ቃዲ፤ የዞህራን ማምዳኒ ወላጅ አባት ፕሮፌሰር ማሕሙድ ማምዳኒ በዚህ ሥራ በዘርፋቸው ለእስልምና መከታ የሆኑትን ያክል ማናችንም ማድረግ የማንችለው ነው ሲሉ አሞግሠዋቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር ማሕሙድ በመጽሐፉ መግቢያ ማስታወሻ ይሁንልኝ ብለው ከጠቀሷቸው ሰዎች መካከል በዚያን ጊዜ የ14 ዓመት ታዳጊ፤ ሰሞነኛው የዓለም መገናኛ ብዙኃን የፊት ገጽ ዞሕራን ማምዳኒ ከፊት ተሰልፏል፡፡ በርግጥ ጓደኞቹም ተጠቅሰዋል፡፡
ልጅዬው ዞሕራን ማምዳኒም ይህን አልዘነጋም፤ ረቡዕ ማለዳ በዓለም ፊት ቆሞ ወላጆቹን “እማዬ እና አባዬ የእናንተ ልጅ በመሆኔ እኮራለሁ። እዚህ የደረስኩት በእናንተ ነው” ሲል ልፋታቸው መክኖ አለመቅረቱን አረጋግጧል። (ሚንበር ቲቪ)












