የሳዑዲ ዐረቢያ የጤና ባለሥልጣናት በአዲሱ ደንብ መሠረት ውስብስብ የጤና ችግር ያለባቸውን የሐጅ ተጓዦች በዘንድሮ ዓመት እንዳይሳተፉ ክልከላ ጥለዋል፡፡ ጥብቅ ቁጥጥር ከሚወሰድባቸው መካከል የካንሠር፣ የልብ፣ የኩላሊት፣ የጉበት፣ የመተንፈሻ አካላት፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ ሥር የሰደደ የሳንባ ሕመም እና ከፍተኛ አደጋ ያዘሉ ይገኙበታል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ያወጡት መመርያ ነፍሰ ጡር ሴቶችን፣ በዕድሜ የገፉ ምእመናን ወይም የማስታወስ ችግር ያለባቸውን እንዲሁም የነርቭ ሕመም እና የሥነ ልቡና ችግር ያለባቸውን ሰዎች አያካትትም፡፡
በዚህ ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት ምእመናን ወደ ሀገሪቱ ከመግባታቸው ወይም በሥነ ሥርዓቱ ከመሳተፋቸው በፊት ሁሉንም የሕክምና ማስረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። ባለሥልጣናት ችግሩን የሚደብቁ ወይም ሐሰተኛ ሠነዶችን የሚያቀርቡ ምዕመናን ከተደረሰባቸው በራሳቸው ወጪ ወዲያውኑ ከሀገር እንዲያባርሩ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሒደት ለሐጅ ጥቅሎች የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ አይደረግላቸውም፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ ሐኪሞች ሐሰተኛ ሰርቲፊኬቶችን እንዳይሰጡ በተናጠል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ጥሰቶችን በተመለከተ የዲሲፕሊን ርምጃ እንደሚወሰድ አስቀድሞ አሳስቧል፡፡ የጤና ባለሥልጣናት ደንቦቹ ተግባራዊ የሚደረጉት የሕዝብ ጤና ሥጋቶችን በመቀነስ ሁሉም ምዕመናን ሥነ ሥርዓቱን ደኅንነቱ በተረጋገጠ መንገድ ማጠናቀቅ እንዲችሉ የታለመ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስትር ተውፊቅ አል ራቢያህ፤ የባለፈው ዐመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ባለፉት 50 ዓመታት ከተከናወኑት መካከል በምእመናን ርካታ በቀዳሚነት የሚቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የሐጅ ተጓዦች ርካታ 91 በመቶ ደርሷል ብሏል፡፡ ይህ የተገለጸው በጂዳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው አምስተኛው ዓለም ዓቀፍ ዓመታዊ የሐጅ ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ጥቅምት 30 የጀመረው የሐጅ ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን፤ ዛሬ ኅዳር 2/2018 ይጠናቀቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












