Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየጆርጅ ቡሽን የፀረ ሙስሊም ዘመቻ ያሸነፈው - ዞሕራን ማምዳኒ

የጆርጅ ቡሽን የፀረ ሙስሊም ዘመቻ ያሸነፈው – ዞሕራን ማምዳኒ

ከ24 ዓመት በፊት እ.አ.አ መስከረም 11/2001፡፡ በዚህ ቀን አሜሪካን ያናወጠው ዜና ተሰማ፡፡ ዜናው በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሲሰራጭ በርካቶች አፋቸውን በእጃቸው ሸፍነው የቴሌቪዥን መስኮታቸው ላይ ከማፍጠጥ ውጪ የሚያደርጉት አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ ሰዎች በቴሌቪዥናቸው ውስጥ በተመለከቱት ክስተት በኒውዮርክ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን እየተንደረደረ ግዙፍ ሕንፃ ላይ ሲሰካ ታየ፡፡ ጉዳዩ በአንድ አውሮፕላን ብቻ አልቆመም፤ ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ሌላ አውሮፕላን እየገሰገሰ መጥቶ በሌላኛው ሕንፃ ላይ ተላተመ። ይህ ሁሉ የሆነው በ149 ደቂቃ ነው።

‘ኤማ ኢ ብሩከር’ በተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለታዳጊዎች መጽሐፍ በማንበብ ላይ የነበሩት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፤ መጀመሪያ ክስተቱ ሪፖርት ሲደረግላቸው ቀለል ተደርጎ ነበር፡፡ ትናንት ኅልፈታቸው የተሰማው ምክትል ፕሬዘዳንት ዲክ ቼኒ ደግሞ ዜናውን የተመለከቱት እንደ አብዛኛው የሀገሬው ሰው በቴሌቭዥን ነው፡፡ ከተማሪዎች ጋር የነበሩት ቡሽ፤ ነገሩ እንደተባለው ቀላል ሳይሆን በመጠን ከፍተኛ መሆኑን ሲረዱ ከነበሩበት ወጥተው ድርጊቱን “ሽብር” ሲሉ ፈረጁት። ክስተቱን ያደረሱትንም “አንለቃቸውም” ብለው መዛቱ የጀመሩት ወዲያውኑ ነው፡፡

በዚህ ቀን ይህ ሁሉ ሲከሰት አንድ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ትምህርት ቤት በክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከደቡብ አፍሪካ ከወላጆቹ ጋር ወደ ኒውዮርክ የመጣውን ታዳጊ አባትዬው እያጣደፈ ወደ ቤት ወሰደው። በጊዜው የሚሆነው ነገር በቅጡ ያልገባው ታዳጊ፣ በወላጁ የተባለውን ከመታዘዝ ውጪ የሚያደርገው አልነበረም። ይህ ታዳጊ ዞህራን ማምዳኒ ይባላል።

ታዳጊው ዞህራን ማምዳኒን አባትየው በጥድፊያ ያመጣው ከስተት 24 ዓመት ሞልቶታል፡፡ የዚያን ጊዜው ታዳጊ አሁን እድሜው 34 ገደማ ደርሷል፡፡ ትውልዱ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ የሆነው ዞህራን ዛሬ ፖለቲከኛ ሆኗል፡፡ ከዚህ አስቀድሞ በብሮንክስ ሁለተኛ ደረጃ የሣይንስ ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን ከቦውዶይን ኮሌጅ በአፍሪካ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውንም አግኝቷል።

ዞሕራን ያደገው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ቡሽ ክስተቱን ተከትሎ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ባስከተሉት ጥፋት ውስጥ ነው። ለጥቃቱ ተጠያቂ የተባሉትን ሁሉንም ማሰር እና ማሰቃየት የአሜሪካ ቀጣዩ ሥራ ነበር፡፡ የጆርጅ ቡሽ አሜሪካ፤ ከዚህ በኋላ በወሰደችው ርምጃ ዋንኛ ሰለባ የሆኑት ሙስሊሞች መሆናቸውን ስለ ጉዳዩ የሚጽፉ ሁሉ ይናገራሉ፡። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ለአሜሪካ ፍትሕ እናሰፍናለን ቢሉም፤ ‹‹ፍትህ›› ሲሉ የጠሩት ጉዳይ ሙስሊሞችን የሚያሳድድ ሆኖ መሰንበቱን ዓለም ተመልክቷል።

የዚያን ጊዜው ታዳጊ ዞህራን በዚህ የመሳደድ ሂደት ውስጥ ነው ዕድሜውን አሳልፏል፤ ቀሪ የታዳጊነት ዕድሜውንና ሙሉ ወጣትነቱን። ይሁን እንጂ ከ24 በኋላ ኒውዮርክን በከቲባነት ለመምራት በዴሞክራቲክ ፓርቲ ለመወዳደር አላመነታም። ይህን ሲያደርግ ለሩብ ምእተ ዓመት ያክል በሀገሩ እሱን መሳይ የእምነት ወንድሞቹ ብዙ ሲደርስባቸው ሳይታዘብ ቀርቶ አይደለም፡፡

ወደ ፖለቲካ ከመግባቱ በፊት በኩዊንስ የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የቤት ባለቤቶች በግዳጅ እንዳይወጡ በመታገል የቤቶች አማካሪ በመሆን የሠራው ዞሀራን፤ እንዲያውም የእስልምና እምነቱን የምርጫ ቅስቀሳው አካል አድርጎታል። በተለያየ ጊዜም ፀረ-ሙስሊም ትርክቶች፣ ጥላቻዎች እና ዘለፋዎች እንደደረሱበት በተደጋጋሚ ተናግሯል። ቢሆንም መደበቅ እንደማይጠቅም ተከራክሯል፡፡ “እንደ ሙስሊም በአደባባይ መቆም ማለት ተደብቀን የምናገኘውን ደኅንነት መስዋዕት ማድረግ እንደሆነ እናውቃለን” ሲል በአንድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተናግሯል፡፡

የመስከረም 11 ክስተት ጧት ላይ በክፍል ውስጥ ባለበት አንድ መምህሩ በዕለቱ አንድ ነገር እንደተከሰተና ነገርዬው እንዳላማረው እንዳስጠነቀቁትም በተለያዩ ቃለ-መጠይቆች ላይ ተናግሯል። ምናልባት የታዳጊው አእምሮው ይህን በቅጡ ሳይመዘግብ አልቀረም፡፡ በነዚህ ሁሉ መነሻ ጥንካሬውን ያሳየው ዞህራን፤ በኒውዮርክ የከንቲባ ምርጫ ትናንት የመጀመሪያው ሙስሊም አሸናፊ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።

ዞሕራን ማምዳኒ ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ ባደረገው ንግግር ለዚህ ላበቁት ሁሉ ምሥጋና አቅርቧል። በኡጋንዳ የተወለደው ማምዳኒ፣ ለድሉ ኢትጵያውያንንም ጭምር አመስግኗል። ለሁሉም ባስተላለፈው መልዕክት – ከእናንተው ነው የወጣሁት፤ የምቆመውም ለእናንተው ነው ሲል ተደምጧል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular