የሕንድ ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ወራት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ በበርካታ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ሙስሊሞች በሚበዙባቸው ሠፈሮች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ በማድረግ፤ መኖሪያ ቤቶችንም በቡልዶዘር አፍርሰዋል፡፡ ለዚህ ምክንያት ያደረጉት ምእመናን “ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እወዳለሁ” ማለታቸውን ለማቆም ፈቃደኞች አልሆኑም በሚል ነው፡፡
የሕንድ ባለሥልጣናት ለእስር ሰበብ ያደረጉትን ይህን ሐረግ፤ ምእመናን በመላ ሀገሪቱ በባነሮች፣ ቲሸርቶች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ላይ አትመው ታይተዋል፡፡ ባለሥልጣናት ይህን ሐረግ መጠቀምን “ኅብረተሰብን ሥጋት ላይ የሚጥል ነው” ብለዋል፡፡ የባለሥልጣናቱ ድርጊት በሰብዐዊ መብቶች ተሟጋቾች ከፍተኛ ትችት እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ይህን ድርጊት “ወለፈንዴ” የሚል ርእስ የሰጠው ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ክስተቱ የጀመረው ነሐሴ 29/2017 በሰሜናዊዋ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኘው ካንፑር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)ን የሚያወድስ የአደባባይ መሰናዶ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ድግሱን ያስተናገደችው ካንፑር፤ በሕንድ ውስጥ በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ግዛቱ በሕንድ ውስጥ በርካታ ሙስሊም ነዋሪዎችን ያቀፈ ነው። የፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በሰሜን ሕንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት እና በሌሎችም ግዛቶች 38 ሰዎች በወቅቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የሲቪል መብቶች ጥበቃ ማኅበር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከነሐሴ የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ በተከታታይ በነበሩ ሦስት ሣምንታት ውስጥ፤ 265 ሰዎች ታስረው በአጠቃላይ 4 ሺሕ 505 ሙስሊሞች በይፋ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ነገር ግን እስራቱን ተከትሎ በበርካታ የሕንድ ከተሞች ሙስሊም ወጣቶች አደባባይ በመውጣት “ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እወዳለሁ” የሚሉ ባነሮችን በሥፋት ይዘው መታየታቸውን ሲቀጥሉ ባለሥልጣናት በምላሹ የኅይል ርምጃ ወስደዋል።
ይህ በእንዲህ ባለበት በምዕራባዊ ኡታር ፕራዴሽ ከተማ ባሬሊ ድርጊቱን በተቃወሙ አንድ ኢማም የተመራው ሰልፍ ወደ ግጭት ከተቀየረ በኋላ ውጥረቱ ተባብሷል። ለዚህ ሰበብ የሆነው በቀጣዩ ቀን ፖሊስ ሰልፈኞችን እና ኢማሙን ብቻ ሳይሆን ዘመዶቻቸውንና ረዳቶቻቸውንም ጨምሮ 75 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ነው፡፡ ግጭቱን ይበልጥ ያባባሰው የአካባቢው ባለሥልጣናት ከተከሳሾቹ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አራት ንብረቶችን በቡልዶዘር ማፍረሳቸው ነው፡፡ ባለሥልጣናት ይህን ሲፈጽሙ ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያም ሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልተሰጠበትም፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሚመራው አገዛዝ ስር፤ ባለሥልጣናት በበርካታ ግዛቶች በተለይም በኡታር ፕራዴሽ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ቤተሰቦች እና አናሳዎችን ቤት በማፍረስ የቅጣት ርምጃ ወስደዋል። በ2024 መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ያለ ተገቢው ሒደት በወንጀል ተሳትፎ ተጠረጥረዋል በሚል ምክንያት” የዜጎችን ንብረት ማፍረስ “ሕገ መንግሥታዊ አይደለም” በሚል እንዲቆም ትእዛዝ ቢያስተላልፍም ባለሥልጣናት ከድርጊታቸው የሚመለሱ አልሆኑም፡፡
ሙስሊሞችን ሰለባ ያደረገው ይህ ድርጊት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ ቁጣን ሲቀሰቅስ፤ በባለሥልጣናት ዘንድ አድልዎ እንዲፈጸም የበለጠ አበረታቷል፡፡ የሕንድ ባለሥልጣናት የተለያዩ ማኅበረሰቦች ሃይማኖታዊ መግለጫዎችን በሚያስተናግዱበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ተቺዎች ጠቁመዋል።
ሙስሊሞች “ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እወዳለሁ” የሚል ባነር እና ቲሸርት በመልበሳቸው ለእስራት በሚዳረጉበት ሕንድ፤ የሒንዱ ሃይማኖታዊ ሰልፎች ብዙውን ጊዜ በፖሊስ ይታጀባሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሄሊኮፕተሮች መንግሥት “የእኛ ናቸው” ለሚላቸው የሒንዱ እምነት ተከታዮች አበባ ያዘንማሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












