– ጠቅላይ ምክር ቤቱ የድርጅቱን ማንነትና የጨረታ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አላደረገ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅና ዑምራ ዘርፍ፤ በዘንድሮ ዓመት ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ይሰጣል ካለው ድርጅት ጋር ውል መፈራረሙን አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ለአገልግሎቱ ውል መፈራረሙን ቢያሳውቅም፤ የአሸናፊውን ድርጅት ማንነትና ለአገልግሎቱ ወጥቷል ያለውን ጨረታ ዝርዝር ጉዳዮች አልገለጸም፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅና ዑምራ ዘርፍ፤ ለሑጃጅ አስፈላጊ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ጋር ውል መፈራረሙን ያስታወቀው ጥቅምት 17/2018 ነው፡፡ በምክር ቤቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ በሠፈረው መረጃ መሠረት፤ የመሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ውስጥ “በጨረታ አሸናፊ ከሆነው ድርጅት ጋር” ውል መፈፀሙን የዘርፉ ተጠሪ ዶክተር ሙሐመድ ሷሊህ ተናግረዋል።
በዚሁ መረጃ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለተወዳዳሪዎች ጨረታውን ያወጣው ጥቅምት 4/2018 መሆኑን ጠቁሟል፡፡ የተመረጠው አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በሚና፣ አረፋ፣ በመካና በመዲና “ለሑጃጅ ምቾት እና ደኅንነት ደረጃዎችን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አቅም እንዳለው” በአወዳዳሪው “በመረጋገጡ” ውል መፈረሙን የዘርፍ ተጠሪው ገልፀዋል። ይሁንና በጨረታው ላይ የተሳተፉትን ድርጅቶችንም ሆነ አሸናፊውን ድርጅት በተመለከተ ይፋ ያደረጉት መረጃ የለም፡፡
ከመረጃው ጋር በተሰራጨው ፎቶግራፍ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ተወካዮች ጋር ውል ሲፈራረም የሚታየው “አልማሲያ” በመባል የሚጠራ ድርጅት አርማ ነው፡፡ ድርጅቱ የሐጅ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ኩባንያ መሆኑን በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ የሐጅን አንግዶች መስተንግዶ፣ ከዓለም አቀፍ የሐጅ ቢሮዎች ጋር መተባበር የሑጃጅን ጉዞ ለማሳለጥ እንደሚሠራም ይገልጻል፡፡ ኩባንያው እንደ ማሌዥያ፣ ሩዋንዳ እና ግብፅ ካሉ የተለያዩ ሀገራት ጋር መሥራቱንም አስፍሯል፡፡
“ሚንበር ቲቪ” በጨረታ አሸንፏል የተባለውን የድርጅቱን ማንነትና የጨረታውን ሒደት ለማጣራት የጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ምላሽ ባለመስጠታቸው አልተሳካም፡፡
የዘንድሮ ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ይከናውናል ተብሎ የሚጠበቀው ከግንቦት 16/2018 እስከ ግንቦት 21/2018 ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ የተጓዙ ምእመናን ቁጥር ስድስት ሺሕ ነበር፡፡ በወቅቱ ከፍተኛውን የምእመናን ቁጥር የላከችው ኢንዶኔዥያ ነች፡፡ ከሀገሪቱ በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተሳተፉት 221 ሺሕ መእመናን ናቸው፡፡ ኢንዶኔዥያ በዘንድሮ ዐመት በሐጅ ክፍያ ላይ ቅናሽ ማድረጓን የሀገሪቱ የሐጅ እና ዑምራ ምክትል ሚኒስትር ዳንሂል አንዛር ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዐመት ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ የከፈሉት 625 ሺሕ ብር ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












