Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየፍልስጤማውያን ተወዳጁ ሰው መርዋን ባርጉውሲ

የፍልስጤማውያን ተወዳጁ ሰው መርዋን ባርጉውሲ

ባለፈው ዓመት ጥር 2017፤ ወቅቱ በሐማስ እና እስራኤል ባለሥልጣናት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የተፈረመበት ነው፡፡ የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ሲደረግ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል አንደኛው በእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ነጻ መውጣት ነው። በስምምነቱ መሠረት ከሚለቀቁት መካከል ከ15 ዓመት በላይ የተፈረደባቸው ግለሰቦች ይገኙበታል። የሐማስ፣ ኳታር እና ግብጽ ባለሥልጣናት ከዚህ ዝርዝር ውስጥ የአንድ ሰው ሥም እንዲካተት እየወተወቱ ነው፡፡

ይህ ግለሰብ እ.አ.አ በ1967 የእስራኤል ጦር በ6ቱ ቀን ጦርነት ዌስት ባንክን በወረራ ሲይዝ የሰባት ዓመት ልጅ የነበረ ነው፡፡ እምብዛም ነገር በማይገለጥበት በዚያ ለጋነት፤ ታላላቆቹ የጎረቤቱ ልጆች የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ በእጃቸው ስለተገኘ ብቻ ድብደባ ሲፈጸምባቸው ተመልክቷል፡፡ ወታደሮቹ ሰውም ሆነ እንስሳ ሳይመርጡ፤ አንድ የጎረቤቱን ውሻ ሳይቀር አንባረቀብን ብለው ጥይት ሲያዘንሙ በልጅ ዐይኑ የተመለከተ ነው፡፡ ይህ ሰው መርዋን ባርጉውሲ ነው፡፡

በተኩስ አቁም ስምምነቱ ከሐማስ አመራሮች በተጨማሪ በኳታር አሚር ተሚም ቢን ሐማድ አል ሳኒ እና የግብጽ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ሐሰን ማሕሙድ እንዲለቀቅ የማግባባት ሥራ የተሠራለት ባርጉውሲ፤ የፍልስጤሙ ፈትሕ ከፍተኛ አመራር ነው፡፡ በወቅቱ ይህን ሰው ለማስፈታት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ደጋግመው ዕድሜ ይፍታህ የፈረዱበት የእስራኤል ባለሥልጣናትም እንደተለመደው የተኩስ አቁሙን ስምምነት በመጣስ በጋዛ የሚፈጽሙትን የዘር ፍጅት ቀጠሉ፡፡

ጥቃቱ በቀጠለበት ወቅት አንድ ጊዜ የጋዛን ነዋሪዎች አስወጥተን ቅንጡ የመዝናኛ ዓለም እንገነባለን፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይህን ሐሳብ ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጋቸውን ሲለፍፉ የሰነበቱት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ መስከረም 19/2018 የጋዛ የሰላም እቅድ ያሉትን ምክረ ሐሳብ ይፋ አደረጉ፡፡ ሃያ ነጥቦችን ባካተተው ዕቅድ በርካታ ጉዳዮች ሲካተቱ፤ አንደኛው ረዥም ዓመታትን በእስር እንዲያሳለፉ የተፈረደባቸው ፍልስጤማውያን እንዲፈቱ የሚደርገው ነበረ፡፡

በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ሥማቸው ከተዘረዘረው መካከል፤ ቀድሞ በተጣሰው የተኩስ ስምምነትና ከዚያም አስቀድሞ ሳይለቀቅ የቀረው መርዋን ባርጉውሲ በድጋሚ ሥሙ ተገኘ፡፡ በርግጥ የዘ ፖፑላር ፍሮንት ፎር ዘ ሊበሬሽን ኦፍ ፕለስታይን መሪው አሕመድ ሳዳት፣ ከፍተኛ የሐማስ አመራሩ ሐሰን ሰልማ እና አሕመድ ባርጉውሲም ሥማቸው ተካቷል፡፡ በተለይ የፈትሕ መሥራች የያሲር አረፋት የቅርብ ሰው እንደነበር የሚነገርለት ባርጉውሲ፤ ይለቀቃል የሚለው ወሬ ሲናፈስ፤ ባለቤቱ ድርድሩ ወደሚደረግበት ካይሮ በረሩ፡፡ ድርድሩ ቀጠለና በትራምፕ የሰላም ሐሳብ ትጥቅ ይፈታል የተባለው የሐማስ መሪዎችም በተኩስ አቁሙ መስማማታቸውን ዓለም ይስማው ብለው በሌላ ጎራ ያሉት የእስራኤል ባለሥልጣናት የሰላም ስምምነቱን ለካቢኔ በማቅረብ እንዲጸድቅ አደረጉ፡፡

በዚህ ጊዜ የባርጉውሲና ሌሎች ሥመ ገናና ፍልስጤማውያን የመብት ተሟጋቾች መፈታት የሚሰምር መሰለ፡፡ ይህን ይበልጥ እውነት ያስመሰለው በአሜሪካ የቀረበው የተኩስ አቁም ሠነድ ላይ የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልኡክ ስቲቭ ዊትኮፍ ፊርማቸውን ማሳረፋቸው ነው፡፡

ነገር ግን የማይገመት ባይሆንም ፍልስጤማውያን የሚፈሩት ደረሰ፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት ከተፈቺዎች መካከል የመርዋን ባርጉውሲን ሥም በምሥጢር እንዲወገድ አደረጉ፡፡ የፈትሕ መሪው ቤተሰቦች የእስራኤል ባለሥልጣናት የባርጉውሲን ሥም ከዝርዝሩ እንዲወገድ ያደረጉት የአሜሪካ የመካከለኛ ምሥራቅ ልዩ ልዑክ በሰነዱ ላይ ከፈረሙበት በኋላ መሆኑን ለመገናኛ ብዙኀን አጋልጠዋል፡፡ ድርጊቱን በፊት አውራሪነት ያስፈጸመው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ የባርጉውሲ ብቻ ሳይሆን የአሕመድ ሳዳት፣ የሐሰን ሰልማ እና አሕመድ ባርጉውሲም ሥም ከዝርዝሩ ውስጥ እንዲሠረዝ ተደርጓል፡፡

እስራኤል ሥማቸውን ከተፈቺዎች ዝርዝር ያስወጣቻቸው መርዋን ባርጉውሲ፤ ከየትኛውም የፍልስጤም ቡድን አመራር በላይ በሀገሬው ሰዎች የሚወደድ መሆኑን የሕዝብ ድምጽ መለኪያዎች ያሳያሉ፡፡

ባርጉውሲ ፈትሕን የተቀላቀለው በ15 ዓመት ዕድሜው ነው፡፡ በዚያው እድሜ የፈትሕ የወጣቶችን ንቅናቄ አንደኛው መሥራች ለመሆን በቅቷል፡፡ በ18 ዓመት እድሜው ለእስራት የተዳረገውም በዚሁ ተሳትፎ ምክንያት ነው፡፡ በእስር ቆይታው ራሱን እስኪስት ድረስ ግርፋትን ጨምሮ በርካታ ስቅይቶች እንደተፈጸመበት በወቅቱ ጽፏል፡፡ ለአስር በተዳረገበት ሰዓት ገና ትምህርቱን ባለማጠናቅቁ እዚያው በነበረበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡ በእስር ቤት ቆይታው የእብራይስጥ ቋንቋ ለማጥናትም አልሰነፈም፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ በኋላ በታሪክ እና ፖለቲካል ሣይንስ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል፡፡ ማስተርሱንም የቀጠለው በተመሳሳይ ፖለቲካል ሣይንስ ነው፡፡  

ባለፉት ሣምንታት ካይሮ ከአደራዳሪዎች ጋር ከነበሩት ከራማላህ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኮባር በተሠኘ መንደር አብሮ አደግ ከሆኑት ኋላም የፈትሕ አመራርና የሕግ ባለሞያዋ ባለቤታቸው ፈድዋ ኢብራሂም ጋር በትዳር የተጣመሩት በ1984 ነው፡፡ ባርጉውሲ ፈድዋን ከማግባቱ በፊት በ18 ዓመቱ ለእስር ሲዳረግ ከወሕኒ ጠብቂኝና ላግባሽ የሚል መልዕክት ሰዶላት ነበር። ይህ ቃል ተፈፅሞ በትዳር አንድ ከሆኑ በኋላም የባርጉውሲ እስር አልቀረም፤ መጀመሪያ ልጃቸውን ሊገላገሉ ሰሞን ባልዬው ታሰረ፡፡ ቢሆንም ቱኒዝያ እና ዮርዳኖስ በስደት በተጓዙበት ጊዜ ያፈሯቸውን አራት ልጆች የማሳደግ ኀላፊነትን ተወጥተዋል።

ፈድዋ፤ ባርጉውሲን ለማስለቀቅ የሚያደርጉት ጥረት በቤንያሚን ኔታንያሁ በተደጋጋሚ ቢደናቀፍም አሁንም ድረስ ግፊቱ ቀጥሏል፡፡ በርግጥ ሰውዬው በፍልስጤማውያን ዘንድ ያለው ተወዳጅነትና ተጽእኖ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕንም አርፈው እንዲቀመጡ አላደረገም፡፡ ትራምፕ በዚህ ሣምንት ለታይም መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ሥሙን አንስተዋል፡፡ የጋዛን አስተዳዳሪ ለመሰየም እየሠሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ትራምፕ፤ በቅርቡ ባርጉውሲን ከእስር ለማስለቀቅ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡

ይህ የትራምፕ ንግግር ከ2002 ጀምሮ በእስራኤል ውስጥ ታስረው የቆዩትን 66 ዓመት እድሜ ላይ የደረሱትን ባርጉውሲን፤ በመጨረሻ ሊፈቱ ይሆን ወይ? የሚል ግምት እንዲሰነዘር ማድረጉ አልቀረም፡፡ ትራምፕ በቃለ ምልሱ አያይዘው የጠቀሱት ማሕሙድ አባስ የሚመሩት የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛውያን እምብዛም የሚወደድ አለመሆኑ፤ ባርጉውሲም ከሙስና የጸዳ፣ ለየትኛውም ፓርቲ የተለየ ተቆርቋሪነት የሌለውና የተለያዩ የፍልስጤም ቡድኖችን አንድ ሊያደርግ የሚችል መሪ ነው የሚል ዕምነት መኖሩ ግምቱን ወደ ዕውነት ያስጠጋው መስሏል፡፡
 
(ለዚህ ጥንቅር ሚድል ኢስት አይ፣ ዝ ኢኮኖሚስት እና አልጀዚራን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular