Homeዜናና ወቅታዊዜናተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የተቀበሩበት ሥፍራ “ማንኛውም ሙስሊም ሲሞት” እንደሚቀበርበት የመዲናዋ እስልምና...

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የተቀበሩበት ሥፍራ “ማንኛውም ሙስሊም ሲሞት” እንደሚቀበርበት የመዲናዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ

  • በአስራ ሁለተኛ መካነ መቃብርነት እውቅና ተሰጥቶታል

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የተቀበሩበት ሥፍራ በመካነ መቃብርነት “እውቅና እንደሰጠው” አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ የተቀበሩበት ሥፍራ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ኮሚሽን በደብዳቤ ቁጥር አ/አ/ፕ/ል/ኮ02/910/2013 በቀን 05/10/13 በተፃፈ ደብዳቤ፤ “ከቅይጥ መኖሪያነት ወደ መካነ መቃብርነት” እንደተቀየረ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

በዚህም ሥፍራውን በአዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙት የሕዝበ ሙስሊሙ መካነ መቃብሮች በመቁጠር “በአስራ ሁለተኛ መካነ መቃብርነት” እውቅና ተሰጥቶታል ብሏል፡፡ አክሎም የመቃብር ሥፍራውን በተመለከተ “ተጨማሪ የማስፋሪያ ጥያቄ ለመንግሥት ከማቅረቡ በተጨማሪ”፤ “እንደሌሎቹ መካነ መቃብሮች ማንኛውም ሙስሊም ሲሞት የሚቀበርበት በመሆኑ” ለመካነ መቃብሩ አስፈላጊው ጥበቃ፣ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ መግለጫው አትቷል፡፡

ከአሁን በኋላ ከመካነ መቃብሩ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት አጀንዳ ሊቆም እንደሚገባ ያሳሰበው ምክር ቤቱ፤ “ውይይትን፣ መማማርንና መተሳሰብን ዓላማ ያላደረጉ” መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በማንኛውም መድረክ እንዳይተላለፉ ጥሪ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውንም “የሕዝቡን አንድነትና ጥቅሞችን የሚጎዱ አካላትንና አካሄዶችን” ፈጽሞ አልታገስም ብሏል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመው ጥቅምት 10/2018 ነበር፡፡ “በኑዛዜ መሠረት” የተከናወነ ነው የተባለው ሥርዐተ ቀብር የተፈጸመው፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቁርአን በሚያቀሩበት ቅጽር ግቢ ነው፡፡

ሥርዐተ ቀብራቸውን ለብቻ በዚሀ ሥፍራ መከናወኑን ተከትሎ፤ እውቅ የእስልምና መምሕራን ባለፈው ሣምንት በተለይ በአዲስ አበባ መስጂዶች ባደረጉት የጁመዐ ኹጥባ፤ ጉዳዩ “መፍትሔ እንዲበጅለት” ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular