ሳዑዲ ዐረቢያን እ.አ.አ ከ1999 አንስቶ በሙፍቲነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሸይኽ ዓብዱልዐዚዝ ቢን ዐብደላህ አልሸይኽ ወደ አኺራ መሻገራቸውን ተከትሎ፤ ሙፍቲ ሸይኽ ዶክተር ሳልህ ቢን ፈውዛንን በተተኪነት ሰይማለች፡፡ “በሥራ ላይ የሚገኙ የአስተዳደር ሕጎች እና ከፍተኛ ሹመቶችንና የቀደሙ ንጉሣዊ ድንጋጌዎችን” መሠረት በማድረግ የተሰጠ ነው ለተባለው አዲሱ ሙፍቲ ሥያሜ፤ የሳዑዲ ፖለቲካዊ መሪው ልዑል ሙሐመድ ቢን ሰልማን ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡ ሹመቱ የተሰጠው በንጉሥ ሰልማን ቢን ዐብዱልዓዚዝ ነው፡፡
አዲሱ ሙፍቲ በሚኒስትር ማዕረግ የሀገሪቱ የከፍተኛ ሊቃውንት ምክር ቤት ሊቀመንበር፣ የሣይንሳዊ ምርምር እና የፈትዋ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በ1354 ዓ.ሂ (እ.አ.አ በ1935) የተወለዱት ሸይኽ ዶክተር ሳልህ ቢን ፈውዛን፤ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በኢማም ሙሐመድ ቢን ሳዑድ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ጭምር በፊቅህ አጠናቀዋል፡፡
የዶክትሬት ጥናታቸው ርእስ “የምግብ ሥርዐት ሕግጋት በኢስላም” የሚል ሲሆን፤ የማስተርስ ጥናታቸው ደግሞ የውርስ ሕጎችን የተመለከተ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት በተጨማሪ ቀድመው በሸይኽ ዐብዱላህ ቢን ሐሚድ፣ በኋላም ሸይኽ ዓብዱልዓዚዝ ቢን ባዝን ጨምሮ በታዋቂ የእስልምና ሊቃውንት ስር እውቀት ቀስመዋል፡፡ ከዚህ በማስከተል በሪያድ ከማስተማር ባሻገር በከፍተኛ የዳኝነት ተቋም ውስጥ ዳይሬክተር በመሆን ሠርተዋል፡፡ በዚያው በሪያድ በሚገኘው የልዑል ሙጠይብ ቢን ዓብዱልዓዚዝ መስጂድ ውስጥ ለአስርት ዓመታት ኢማምና ኻጢብ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ሸይኽ አል ፈውዛን ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ምላሸ እና ማብራሪያዎች በሚሰጥበት፤ ከሠላሳ ዓመት በላይ በራድዮ ሞገድ ላይ በቆየው፤ “ኑሩን አለደርብ” የተሰኘ ፕሮግራም ላይ ለረዥም ጊዜ በመሳተፋቸው ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኅን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ከራድዮ ዝግጅት ባሻገር መጻሕፍትንም አዘጋጅተዋል፡፡
ሸይኽ አል ፈውዛን ባገኙት አዲስ ሥያሜ የሳዑዲ ዐረቢያ የሃይማኖት ተቋማት መሪ በመሆን የፈትዋ አወጣጥ እና ምሑራዊ ምርምሮችን በበላይነት ይቆጣጠራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












