የዮርዳኖስ የደኅነነት መሥሪያ ቤት፤ ባለፉት ዓመታት ለጋዛ አጋርነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ዜጎችን በማፈን ምርመራ እንደሚያካሄድ የመካከለኛውን ምሥራቅ ውሎ እና አዳር የሚዘግበው ሚድል ኢስት ዐይ ከበርካታ ምንጮች ማጣራት ችያለሁ ብሎ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በዘገባው መሠረት፤ “ጂአይዲ” ተብሎ የሚጠራው የሀገሪቱ አጠቃላይ የስለላ መምርያ የሚመራው ሠፊ ዘመቻ፣ እስራኤል በጋዛ ለምትሰነዝረው ጥቃት ሰለባዎች የገንዘብ ልገሣና ሌሎች የዓይነት ድጋፎችን የሚያሰባስቡ አክቲቪስቶችንና አስተባባሪዎችን ዒላማ ያደረገ ነው። በዚሁ አግባብ በደኅንነት ሰዎች ቁጥጥር ስር የነበረ አንድ ታሳሪ “ዘመቻው ከዮርዳኖስ ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ የለም፤ ለእስራኤል ጥቅም የሚደረግ ነው” ብሏል፡፡
ሥማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የዮርዳኖስ የፖለቲካ ምንጭ እንዳሉት፤ ከእስር ዘመቻው ጀርባ ሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች አሉበት፡፡ ዘመቻውን የምታስፈጽመው ዮርዳኖስ ደግሞ በምላሹ ከሪያድ እና ከአቡዳቢ የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት ግብ አስቀምጣለች፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በሕግ አግባብ ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ በዜና ምንጩ የተጠቀሱ በርካታ እስረኞች እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ እስረኞች ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ማንም ሰው የተፈጸመባቸውን ሳያውቅ ተለቀዋል። የደኅነት ሰዎች ታሳሪዎቹን ሲለቋቸው የቆዩበትን የእስር ሁኔታ ለማንም እንዳይናገሩ ማሳሰቢያ ሰጥተው ነው የለቀቁት፡፡
በምርመራ ወቅት አብዛኞቹ እስረኞች ከፍልስጤም ጋር ያላቸውን አጋርነት በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ ይህም በፍልስጤም ግዛት ውስጥ ለሚገኙ የጥቃቱ ሰለባዎች ልገሣዎችን፣ የገንዘብ ድጋፍን ወይም የርዳታ ቁሳቁሶችን የተመለከተ ነው፡፡
ድረ ገጹ በአሁኑ ሰዓት በጋዛ አጋሮች ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ዘመቻ በዮርዳኖስ እ.አ.አ በ1989 “የዲሞክራሲ ሽግግር” ከተደረገ በኋላ በዚህ መጠኝ ታይቶ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በዘገባው ላይ የተጠቀሱት ሀገሮች በፍልስጤም ደጋፊዎች ላይ ስለሚፈጽሙት ምርመራ የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












