የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 9/2017 በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ የዘንድሮ ምርጫ የሚከናወንበትን የጊዜ ሠሌዳ ይፋ አድርጓል፡፡ የቦርዱ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ ምርጫው የሚካሄደው ከነሐሴ 9/2017 እስከ ነሐሴ 11/2017 ድረስ ነው፡፡
የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ተጠናቆ ወደሚቀጥለው የምርጫ ተግባር መገባት እንዳለበት ውሳኔ መተላለፉን የገለጹት የቦርዱ ኃላፊዎች፤ በቀዳሚው ቀን ነሐሴ 9/2017 የሚከናወነው የእስልምና ሊቃውንት ምርጫ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ቀን ዑለማዕ በየመስጂዱ ከጁመዓ ሰላት በኋላ በመስጅዳቸው ተገናኝተው ምርጫቸውን ያከናውናሉ፡፡ በቀጣይ ቀናት የተቀሩትን የምሑራን እና የወጣቶች ምርጫ ነሐሴ 11/2017 ከእኩለ ቀን በፊት እንደሚያካሄድ ተጠቁሟል፡፡

በመግለጫው መሠረት፤ ከምርጫ አስቀድሞ ባለው ሣምንት የእጩዎች ግምገማና መለያ የሚሆነው አምስት የሹራ ቀናት እንደሚኖር በመግለጽ፤ “የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለመጅሊስ ምርጫ ሹራ የሚያደርግበት” ተብለው የተለዩት ቀናት ከሐምሌ 30/2017 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 4/2017 ድረስ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡

በእነዚህ ቀናት በሁሉም ዘርፍ ተመራጮችን መራጩ ማኅበረሰብ በሚያደርገው ምክክር እንደየምዝገባ ክፍሉ በተቀመጡት ዘርፎች ማን እንደሚመረጥ “ተዋውቆ፣ ተወያይቶ እና ለይቶ በልቦናው ተመራጩን የሚያውቅበት ጊዜ” ይሆናል፡፡ ከነሐሴ 5/2017 እስከ ነሐሴ 8/2017 ድረስ ሁሉም ተረጋግቶ ከምርጫ ምዝገባ ውይይት ረፍት በመውሰድ በጥሞና፣ “በዱዓዕ፣ በፍቅር፣ በሠላም ለምርጫ ቀን የሚዘጋጅባቸው ቀናት ይሆናሉ” ተብሏል፡፡
በመግለጫው የመጅሊስ ምርጫ ተጠናቆ ነሐሴ 30/2017 የጠቅላይ ምክር ቤቱ ጉባኤ ተካሄዶ የሥራ አስፈጻሚ ፕሬዝዳንትና ሌሎች ኃላፊዎችን እንደሚመርጥ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚኖሩ ሁለት ቀናት ተመራጩ አመራር ከነባሩ የመጨረሻ አመራር ርክክብ ይፈጽማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኃላፊዎች የመጨረሻውን ሒደት ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ በዘንድሮ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን በአራት ክላስተር በመክፈል ሒደቱን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በዚህም በሰሜናዊ ክላስተር አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር እና ቤንሻንጉል፣ በደቡባዊ ክላስተር ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን፣ በምሥራቃዊ ክላስተር ሱማሌ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን፣ በማዕከላዊ ክላስተር ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተካተዋል፡፡
ቦርዱ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ፤ ከሰኔ 13/2017 አንስቶ ላለፉት ሣምንታት ሲከናውን በቆየው የመራጮች ምዝገባ፤ ቀድሞ ከተጠበቀው 60 በመቶ ማሳካቱን በማንሳት ምዝገባው የፊታችን እሑድ ሐምሌ 13/2017 እንደሚጠናቀቀቅ በማስታወቅ በቀሪ አምስት ቀናት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሙስሊሞች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)
(ከቆይታ በኋላ በዚህ ዜና ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል)












