Homeዜናና ወቅታዊዜናዓለም አቀፉ ሥርዐት ፍልስጤማዊያንን “ከሚፈጸምባቸው በደል መከላከል አልቻለም” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች...

ዓለም አቀፉ ሥርዐት ፍልስጤማዊያንን “ከሚፈጸምባቸው በደል መከላከል አልቻለም” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ነቀፌታ ሠነዘሩ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔዚ፤ ዓለም አቀፉ ሥርዐት “ፍልስጤማዊያንን ከሚደርስባቸው በደል መከላከል አልቻለም” ሲሉ ነቀፌታ የሰነዘሩት የጋዛን የዘር ፍጅት ለማስቆም ተግባራዊ ርምጃዎችን የመውሰድ ዓላማ ባለው በአስቸኳይ በተጠራ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ በኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ ማክሰኞ የተጀመረው ጉባዔ በዛሬው እለት ይጠናቀቃል፡፡

አስተናጋጇ ኮሎምቢያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባስተባበሩት ጉባኤ ላይ፤ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ በከፈተችው የዘር ማጥፋት ክስ ዙርያ የተሰባሰቡት “የሔግ ቡድን” በሚል ሥያሜ የሚጠሩ ሀገሮች ስብስብ ዋንኛ ተሳታፊ ሆኗል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት አልባኔዚ፤ ዓለም አቀፉ ሥርዓት የፍልስጤምን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል አለመቻሉን ጠቅሰው ነቀፌታ ከመሰንዘራቸው ባሻገር፤ ዓለም አቀፍ ሕግ “ደካማ” ተብለው የተፈረጁትን መታደግ አልቻለም ብለዋል፡፡

አልባኔዚ በተመሳሳይ ከቀናት በፊት በዘር ፍጅት ይነግዳሉ ያሏቸውን 60 የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎችን ያጋለጠ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርጉ ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት በኩባንያዎቹ ላይ ምርመራ እንዲጀምር ጥሪ በማቅረብ ነው፡፡ በሪፖርቱ ከጠቀሷቸው ኩባንያዎች መካከል ግዙፉ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት እና አማዞን ተካተዋል፡፡ ይህን ማጋለጣቸውን ተከትሎ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሀገራቸው በአልባኔዚ ላይ ማእቀብ መጣሏን አሳውቀዋል፡፡  

ስለ ጉዳዩ በቦጎታ ጉባዔ ላይ ያነሱት የሕግ ባለሞያዋ፤ ማእቀቡ በእኔ ላይ በግል የተጣለ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍትሕ እና ነፃነት ጎን በመቆም ለመከላከል የሚሞክሩትን ለማስበርገግ የተላለፈ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ “ይህ ስለ እኔ ወይም ስለሌላ ማንኛውም ግለሰብ ሳይሆን” እጅግ ወሳኝ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ ላይ ለሚገኙት “ለፍልስጤም ሕዝቦችና ስለ ፍትሕ የሚደረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሀገሮች ዝምታቸውን ሰብረው በመጨረሻም “በቃ” በማለት አሁንም ወደ ሕጋዊ መስመር የመመለስ ዕድል እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በበጎታው ጉባዔ ላይ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔዚ በተጨማሪ የፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ልዑክ ሪያድ መንሱር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ለሔግ ቡድን ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

የሔግ ቡድን በመባል የሚጠራው ስብስብ በጥር ወር 2025 በኔዘርላንድስ ከተማ ሔግ ከተማ ሲመሠረት፤ ዓላማው እስራኤልን በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ የስብስቡ ዘጠኝ መሥራቾች ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ፣ ማሌዥያ፣ ቦሊቪያ፣ ኩባ፣ ሆንዱራስ፣ ናሚቢያ፣ እና ሴኔጋል ናቸው።

አንደኛዋ አባል ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በታኅሣሥ 2023 በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) በእስራኤል ላይ የመሠረተችው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ፤ ከ20 በላይ ሀገሮችን ድጋፍ ማግኘቱን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular