Homeዜናና ወቅታዊዜናየፈረንሣይ እና ቤልጅየም የሕግ ባለሞያዎች በጋዛ “የዘር ፍጅት ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ባለመቻሉ”...

የፈረንሣይ እና ቤልጅየም የሕግ ባለሞያዎች በጋዛ “የዘር ፍጅት ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ባለመቻሉ” በአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ላይ ክስ ሊመሠርቱ ነው

የፈረንሣይ እና ቤልጅየም የሕግ ባለሞያዎችን ያቀፈ ቡድን፤ በጋዛ ከተማ በፍልስጤማውያን ላይ “የዘር ፍጅት ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ባለመቻሉ” በአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ላይ ክስ የሚመሠርተው ዛሬ ሐሙስ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ክሱ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤትን የሚያካትት ነው፡፡

የባለሞያዎች ቡድኑ ክስ የመጣው፣ የኅብረቱ ሚኒስትሮች ማክሰኞ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት እና የእስራኤል ስምምነት እንዲታገድ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ማስማማት ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ ነው፡፡ በዕለቱ በብራስልስ የተሰባሰቡት የ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በኅብረቱ እና በእስራኤል የሽርክና ስምምነት ላይ የሠፈሩ ድንጋጌዎች እንደተጣሱ ቢረጋገጥም ሊወሰዱ በሚችሉ ርምጃዎች ላይ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡

በአማራጭነት ከቀረቡት ርምጃዎች መካከል ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ፣ የንግድ ልውውጦች እንዲቆሙ፣ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣል እና በእስራኤላዊ ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ መጣልን ያካትታል፡፡  

በሉክሰምበርግ የሚከፈተው ክስ ሁለቱ የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት በጋዛ ውስጥ እየተፈጸሙ የሚገኙትን ከባባድ ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ርምጃ ባለመውሰዳቸው የሚመሠረት የመጀመሪያው ይሆናል፡፡ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ያቀረበው በፈረንሣይ የሚንቀሳቀሰው ‘ጁሪስትስ ፎር ዘ ሪስፔክት ኦፍ ኢንተርናሽናል ሎው’ የሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፤ ቀደም ብሎ ለኮሚሽኑ እና ለምክር ቤቱ ይፋዊ ማሳወቂያዎችን መላኩን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡

የሕግ ባለሞያዎቹ ባቀረቡት ክስ የአውሮፓ ኅብረት የዘር ማጥፋትን የመከላከልና የፍልስጤም ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን የሚከለክሉ መሰናክሎችን የማስወገድ ግዴታ፤ በተለይ ደግሞ የጦር ወንጀሎችን እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን የማክበር ግዴታን በተመለከተ ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆዎችን ጥሷል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ቡድኑ ፍርድ ቤቱ የጥንቃቄ ርምጃዎችን በተመለከተ ውሳኔ እንዲያሳልፍም እየጠየቀ እንደሚገኝ ለዜና ምንጩ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከእስራኤል ጋር የገቡት ስምምነት እንዲታገድ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ማስማማት ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ፤ በተመሳሳይ በኮሎምቢያ ቦጎታ በተካሄደው የጋዛን የዘር ፍጅት ለማስቆም ተግባራዊ ርምጃዎችን የመውሰድ ዓላማ ባለው በአስቸኳይ በተጠራ ጉባዔ ላይ ትችት አስተናግደዋል፡፡ ትችቱን የሰነዘሩት ከቀናት በፊት በዘር ፍጅት ይነግዳሉ ያሏቸውን 60 የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎችን ያጋለጠ ሪፖርት ይፋ ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔዚ ናቸው፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ከእስራኤል ጋር ያለውን ሽርክና ለማቋረጥ ከስምምነት ላይ ባይደርስም እስራኤል በጋዛ ላይ የምትሰነዝረውን ጦርነት ስፔን፣ አየርላንድ እና ስሎቬንያን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባላት የዘር ፍጅት ወንጀል ነው ሲሉ ፈርጀውታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular