Homeዜናና ወቅታዊዜናየመጅሊስ ሥራ አስፈጻሚ የሥልጣን ዘመን ይራዘም ይሆን?

የመጅሊስ ሥራ አስፈጻሚ የሥልጣን ዘመን ይራዘም ይሆን?

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት ሦስተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 እያካሔደ ይገኛል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ አዳራሽ እየተከናወነ በሚገኘው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ዓብዱልከሪም ሸይኽ በድረዲን፣ ዋና ጸሐፊው ሸይኽ ዋና ሐሚድ ሙሳ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የ2017 በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ከማድረግ ባሻገር በሌሎች አስቸኳይ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል የወቅቱ ሥራ አስፈጻሚ የሥልጣን ዘመን ማራዘምን የተመለከተው እንደሚገኝበት ተሰምቷል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተጠራው የምክር ቤቱ የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ የዘንድሮ ምርጫ የሚከናወንበትን የጊዜ ሠሌዳ ይፋ ባደረገ ማግሥት ነው፡፡ የቦርዱ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ ምርጫው የሚካሄደው ከነሐሴ 9/2017 እስከ ነሐሴ 11/2017 ድረስ ነው፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ዓብዱልዓዚዝ ኢብራሂም (ዶ/ር) ረቡዕ ሐምሌ 9/2017 በሰጡት መግለጫ፤ የመጅሊስ ምርጫ ተጠናቆ ነሐሴ 30/2017 የጠቅላይ ምክር ቤቱ ጉባኤ ተካሄዶ የሥራ አስፈጻሚ ፕሬዝዳንትና ሌሎች ኃላፊዎችን እንደሚመርጥ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖሩ ሁለት ቀናት ተመራጩ አመራር ከነባሩ የመጨረሻ አመራር ርክክብ ይፈጽማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአመራር ርክክብ የሚደረግበትን ቀን በይፋ አልገለጹም፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን የወጡት በ2014 እንደነበር ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው ሦስት ዓመት የሥልጣን ጊዜ በተያዘው ሐምሌ ወር ይጠናቀቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular