የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤናው ዘርፍ ባለሥልጣናት ይፋ ባደረጉት መረጃ፤ እ.አ.አ በ2024 ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገሮች ከ14 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ምንም አይነት ክትባት ማግኘት አልቻሉም ተብሏል።
ይህ ይፋ የተደረገው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለውን ዓመታዊ የክትባት ሽፋን ትንበያ የተመለከተ ሪፖርት ዛሬ ማክሰኞ በዓለም የጤና ድርጅት እና በሕፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ በኩል ይፋ ሲደረግ ነው፡፡
በሪፖርቱ ላይ ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ማግኘት አልቻሉም ከተባሉት መካከል ኩፍኝ፣ የልጅነት ልምሻ፣ ዲፒቴሪያ የተሰኘ ተላላፊ የጉሮሮ በሽታ፣ ትክትክና መንጋጋ ቆልፍ ይገኙበታል፡፡
በ2024 ለእነዚሁ በሽታዎች መከላከል የሚውሉ የመጀመሪያ ደረጃ ክትባቶች ለሕፃናቱ ተደራሽ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ያመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት፤ ለሕፃናት መሰጠት ከነበረበት ሦስተኛ ደረጃ ክትባት 85 በመቶው ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡ ባለሥልጣናቱ ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጡት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የርዳታ አቅርቦት መቋረጡን ነው፡፡
በተለይ ባለፈው ጥር 2025 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት መውጣቷን ይፋ ካደረጉ በኃላ፤ በሀገሪቱ የተራድኦ ድርጅቱ ዩኤስ ኤ አይ ዲ በኩል ለዓለም ሲቀርብ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቆም ተደርጓል። በዚህም ምክንያት በአሜሪካ በኩል ለጤናው ሥርዓት እና ለሰብዓዊ ርዳታ ይመደብ የነበረው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ እንዲቋረጥ አሊያም ሳይሰጥ እንዲጓተት በመደረጉ በዘርፉ የሚደረገውን ድጋፍ በእጅጉ ለችግር አጋልጦታል ተብሏል፡፡
ክትባት ሳይሰጥ በመቅረቱ የሕፃናት ጤና ሥጋት አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱ ሀገሮች መካከል ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ናይጄሪያ፣ ሕንድ፣ ሱዳን፣ ኮንጎ፣ ኢንዶኔዥያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን እና አንጎላ ተዘርዝረዋል፡፡ በመላው ዓለም ለኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት 76 በመቶ ተደራሽ ማድረግ ቢቻልም፣ተላላፊ በሽታዎች በሚፈለገው ደረጃ ለመከላከል 95 በመቶ በላይ የክትባት ሽፋን እንደሚያስፈልግ የመንግሥታቱ ድርጅት የጤና ባለሞያዎችን ጠቅሶ አሸርቅ አል አውሰጥ ዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












