Homeዜናና ወቅታዊዜናዓለም አቀፉ የሐላል ኢኮኖሚ በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት የዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ሰንሰለት...

ዓለም አቀፉ የሐላል ኢኮኖሚ በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት የዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ ቢገጥመውም ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት አስመዝግቧል – ጥናት

ዓለም አቀፉ የሐላል ኢኮኖሚ በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት የዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ ቢገጥመውም፤ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት አስመዝግቧል ሲል ያሳወቀው “ዲናር ስታንዳርድ” የተሰኘ የጥናት እና ምርምር ድርጅት ነው፡፡

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሐላል ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር ጥናት የሚሠራው ድርጅት ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት፤ ሙስሊሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሸሪዓ መርሆች ጋር ተስማሚ በሆኑ ምርት እና አገልግሎት ላይ ፈሰስ ያደረጉት የገንዘብ መጠን 1 ነጥብ 77 ትሪሊዮን ፓዉንድ ደርሷል፡፡ ዘርፉ በግጭቶች ምክንያት በተከሰተው የዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ ጫናውን በመሸከም አስደናቂ የመቋቋም አቅም ማሳየቱንም ጥናቱ አመልክቷል፡፡

የጥናቱን ሪፖርት በተመለከተ የተናገሩት የዲናር ስታንዳርድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ራፊዑዲን ሺኮህ፤ “የእስላማዊ ኢኮኖሚ እያደገ ብቻ አይደለም፤ እየተለወጠም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም “በሙስሊም ሸማቾች ባሕርይ ላይ ዓለም አቀፍ ገበያዎችን የሚቀይር መሠረታዊ ለውጥ እየተመለከትን ነው” ሲሉ ስለ ቀጣዩ ጊዜ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ ጥናት ላይ የእስላማዊ ፋይናንስ አጠቃላይ የሐብት ምጣኔ በ9 ነጥብ 2 በመቶ በማደግ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ፓዉንድ መድረሱ ተገልጿል፡፡ በሐላል ኢኮኖሚ ማሌዥያ የዓለማችን መሪ ሀገር ሆና ስትቀጥል፤ ዩናይትድ ኪንግደም ዕድገት በማስዝገብ ሥሟ ተጠቅሷል፡፡ በሐላል ኢኮኖሚ ከታቀፉት ውስጥ ሐላል ምግብ ከፊት ሲሰለፍ፤ መዋቢያዎች እና ሥነ ምግባርን የጠበቁ ብራንዶች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡

ሪፖርቱ እስራኤል በጋዛ ላይ የወሰደችውን ወታደራዊ ርምጃ ተከትሎ የምርት ተጠቃሚዎች የሸመታ አዝማሚያ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደተስተዋለ ይገልጻል። በዚህም ኔስሌ፣ ማክዶናልድ እና ኮካ ኮላ ሙስሊም ሸማች በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የገበያ መቀዛቀዝ አስተናግደዋል፡፡ በአንጻሩ የግብፁ ለስላሳ መጠጥ ቪ7 ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች የሚልከው ምርት በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ በእንግሊዝ የሚመረተው ጋዛ ኮላ በተጀመረ በወራት ውስጥ ከ500 ሺሕ በላይ ቆርቆሮዎችን ሸጧል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያመለከተው፤ የሐላል ኢኮኖሚ በሙስሊም ተጠቃሚዎች ዘንድ ዕድገት ከማስመዝገቡ ባሻገር የሐላል የምስክር ወረቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከግብይት ደኅንነት እና ጥራት ጋር እየተዛመደ ይገኛል፡፡ በዚህም ሙስሊም ያልሆኑ ተጠቃሚዎችም ወደ ሐላል ምርቶች እየተሳቡ ነው፡፡ ለዚህ በአብነት የተጠቀሰው በሕንድ ገበያ ውስጥ ሐላል መዋቢያዎች ቀድሞ ገበያውን ተቆጣጥረው የቆዩና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ምርቶችን እየተቀናቀኑ መምጣታቸው ነው፡፡

ሐላል መዋቢያ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት ከሐላል ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ድርሻ ቢይዝም ዲናር ስታንዳርድ ግን ሙስሊሞች በሐላል የመዋቢያ ዕቃዎች ላይ የሚያወጡት ወጪ እ.አ.አ በ2028 ከ86 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ሊደርስ እንደሚችል ግምት አስቀምጧል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ይሆናል ብሎ ያስቀመጠው፤ ወጣት ሸማቾች መዋቢያዎች ወደ ገበያ ከመውጣታቸው አስቀድሞ በእንስሳት ላይ ያልተፈተኑ እና ከጎጂ ኬሚካሎች ነጻ የሆኑ የግል እንክብካቤ ዕቃዎችን እየመረጡ በመምጣታቸው መሆኑን የሐላል ታይምስ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ዓለም አቀፉ የሐላል ኢንዱስትሪ ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ከ2028 በፊት 10 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። በአሁኑ ወቅት ከዓለም የሕዝብ ቁጥር የሙስሊሞች ቁጥር አንድ አራተኛ የሚገመት ነው፡፡ ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ2050 ወደ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን በየጊዜው መጨመሩ ለገበያው እምቅ አቅም መሆኑንም የዘርፉ ባለሞያዎች ይገልጻሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular