የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፤ በተያዘው የ2017 ክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እና የተጎጂ ይሆናሉ ተብሎ የተለዩ አካባቢዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ አዋሽ ወንዝን ተከትሎ የሚኖሩ ከመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል፣ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ጀምሮ እስከ ታችኛው አዋሽ አካባቢዎች በተለይም በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ዳር የሚገኙ ወረዳዎች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች ወረዳ ሆሞራቴ ከተማን ጨምሮ፣ በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ እና ሌሎች በባሮ ወንዝ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉት ወረዳዎች፣ እንዲሁም በዋቤ ሸበሌ ወንዝ ሊጠቁ የሚችሉ የሶማሌ ክልል ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በጣና ሀይቅ አቅራቢያ የሚገኙ አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚህ የክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እና ተጎጂ ይሆናሉ በሚል መለየታቸውን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከተሞች በመሉ ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት በየትኛውም ጊዜ በቅዕበታዊ ጎርፍ አደጋ ሊጠቁ እንደሚችሉ በመጠቆም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ባልታሰቡ ክስተቶች እና ትናንሽ ወንዞች ምክንያት የጎርፍ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡
ዓለም አቀፍ ትንበያዎችን በመጥቀስ በእነዚህ ክልሎች እና ሌሎችም ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ይህንን ተከትሎ የክረምት ወቅት በተለያዩ ዓመታት የጉዳቱ መጠን ቢለያይም በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋ በመከሰት በሕይወትና በንብረት ላይ የተለያዩ አደጋዎች ሊደርስ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ አደጋውን በወቅቱ በመገንዘብ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላትና ማኅበረሰቡ ዝግጅት እንዲያደርግ እንዲሁም ቀድመው ርምጃ እንዲወሰዱ አሳስቧል፡፡
የጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የተለዩት በተፋሰስና ወንዝ ዳርቻ አዋሽ ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ ተከዜ፣ ባሮ፣ ኦሞ እና የከተሞች ወንዞች፣ በግድቦች ማስተንፈሻ አካባቢዎች፤ ተንዳሆና ቀሰም፣ ግልገል ጊቤ ፣ ተከዜ፣ ገናሌ፣ ዳዋ ፣ ፊንጫ እና ቆቃ፤ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆነ አካባቢዎችና ከተሞች መሉ በሙሉ ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት በየትኛዉም ጊዜ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊጠቁ ስለሚችሉ ማህበረሰቡ፣ የሚመለከታቸው ተቋማትና የአስተዳደር መዋቅሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄና በክትትል ላይ ተመሰረተ እርምጃዎች እንዲወስዱም በኮሚሽኑ መረጃ ላይ ተጠቅሷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












