Homeዜናና ወቅታዊዜናአሚን ስኩል አዋርድ በአወሊያ አካዳሚ ተካሄደ

አሚን ስኩል አዋርድ በአወሊያ አካዳሚ ተካሄደ

በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚካሄደው በ‎አቢሲንያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት፤ አቢሲንያ አሚን በኩል የሚዘጋጀው ‘አሚን ስኩል አዋርድ’ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 5/2017 በአወሊያ አካዳሚ ቀጥሎ ተከናውኗል።
‎
በትምህርት ቤቱ በተዘጋጀው መርሐ ግብር፣ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ መምህራን ማበረታቻ ተበርክቷል። በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የአቢሲንያ አሚን ብራንድ አምባሳደር ሙሐመድ ፈረጅ ተገኝተዋል።
‎
‎ባንኩ የገንዘብ ሽልማት ያበረከተላቸው ተማሪዎች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከየክፍል እርከኑ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው።
‎
‎ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች እንደየደረጃቸው ከአራት ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ ብር የተበረከተ ሲሆን፣ ከስድስተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ላሉት ደግሞ በተመሳሳይ ከስድስት ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ ብር አበርክቷል።
‎
‎በሽልማት ሥነ ሥርዐቱ ላይ ከየክፍል እርከኑ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት ተማሪዎች ውጪ፤ ከሁሉም ክፍሎች ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበው ተማሪ በልዩ ሁኔታ የ10 ሺሕ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ከአቢሲንያ አሚን ተበርክቶለታል፡፡
‎
‎ከተማሪዎች በተጨማሪ የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው ለሶስት መምህራንም ሽልማት አበርክቷል፡፡ በአቢሲንያ አሚን ለመምህራኑ አስር ሺሕ ብር ተበርክቷል።
‎
‎በሽልማት ስነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት ዋና የአቢሲንያ ባንክ አቢሲንያ አሚን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ኦፊሰር አቶ ዓብዱልቃድር ሪድዋን፣ አቢሲንያ አሚን ሸሪዓን መሠረት ባደረገ መልኩ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የኢትዮጵያን የትምህርት እድገት በመደገፍ፣ ልህቀትን በማጎልበት እንዲሁም ብቁ ተረካቢ ዜጋ በማፍራት ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
‎
‎አክለውም ባንኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት እና ከፍተኛ የሐብት አሰባሰብ በማስመዝገብ በማህበረሰቡ ዘንድ ተመራጭ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሲጪ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ባንኩ አሁን ላይ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት ሥራውን ከማጎልበት ባሻገር፣ ዘመኑን የሚመጥን ዲጂታል ግብይትና ከወረቀት ነፃ (Paperless) የሆኑ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ባንኩ የሚያቀርበው የማበረታቻ ሽልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የትምህርት እድገት ለመደገፍ፣ ልህቀትን ለማጎልበት እና ብቁ ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት ያለመ መሆኑን አስገንዝበው፣ ተሸላሚዎቹ ለሀገራቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለትምህርት ቤታቸው ኩራት እንዲሆኑ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
‎
‎አቢሲንያ አሚን የሚያዘጋጀው አሚን ስኩል አዋርድ በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት በኮርዶቫ ፣ ረዛን እና ነጃሺ ትምህርት ቤቶች በ2017 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡
‎
‎አቢሲንያ አሚን በአዲስ አበባ ከተማ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሌሎች የክልል ከተሞች በአጠቃላይ በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለተማሪዎችና መምህራን የሚያበረክተውን የማበረታቻ ሽልማት እንደሚቀጥል አስታውቋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular