Homeዜናና ወቅታዊዜናፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን የበድር ኢትዮጵያ አባል ድርጅት ሆኖ ለመቀላቀል ውሳኔ ማሳለፉን ይፋ...

ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን የበድር ኢትዮጵያ አባል ድርጅት ሆኖ ለመቀላቀል ውሳኔ ማሳለፉን ይፋ አደረገ

መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፤ የበድር ኢትዮጵያ አባል ድርጅት ሆኖ ለመቀላቀል ውሳኔ ማሳለፉን በይፋ አስታውቋል፡፡ ፋውንዴሽኑ፤ በድር ኢትዮጵያን ለመቀላቀል ውሳኔ ማሳለፉን የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ጀማል ያሲን ሰኔ 30/2017 በጻፉት ደብዳቤ አረጋግጠዋል፡፡

“ሚንበር ቲቪ” በተመለከተውና በፕሬዝዳንቱ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ በሠፈረው መሠረት፤ ፋውንዴሽኑ የበድር ኢትዮጵያ አባል ድርጅት ሆኖ ለመቀላቀል ውሳኔ ያሳለፈው፤ “ጊዜ ከወሰደ የጋራ ምክክር በኋላ” ነው፡፡ ውይይቶች የተካሄዱት “በአንድነት፣ በግልፅነት እና የሰፊውን ዑማ ደኅንነት ባስጠበቀ” አኳኋን እንደነበር የገለጸው ደብዳቤው፤ በዚህ ሒደት “የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች” በግልፅ ማሳወቁንም ይገልጻል፡፡ ድርጅቱ ይህን ሲያቀርብ በድር ኢትዮጵያ አሳይቷል ላለው “የትብብር መንፈሥ እና ያለፉትን ልዩነቶች ለመፍታት ለያዘው ቁርጠኛ አቋም” ምሥጋና አቅርቧል፡፡

ፈርስት ሂጅራ “በጋራ መከባበር እና በአንድ ራዕይ በመተባበር ለኅብረተሰቡ እና ለመላው ዑማ ጥቅም በቅን ልቦና በመተባበር ወደፊት ለመራመድ” ከበድር ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱንም ገልጿል፡፡

ከበድር ኢትዮጵያ ጋር ባንድነት ለመሥራት መስማማቱ የገለፀው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፤ በአሜሪካ በዋሽንግተን ሜትሮ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተመሠረተው እ.አ.አ በ1986 ነው፡፡ ቀድሞ በምሥረታው ወቅት “የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ፋውንዴሽን” ተብሎ ይጠራ የነበረው ድርጅት፤ ሥያሜውን “ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን” በሚል የለወጠው በ1995 ነው፡፡ ሥያሜውን መለወጥ ያስፈለገው ከኢትዮጵያና እስልምና ታሪክ ጋር ትስስር በመፍጠር ታሪክን ለማነቃቃት በሚል ዓላማ መሆኑን በድረ ገጹ ላይ የሠፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሁለቱ አንጋፋ የሙስሊሞች ድርጅቶች ባንድነት ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን፤ በተመሣሣይ በድር ኢትዮጵያ በካናዳ ከሰኔ 26/2017 እስከ ሰኔ 29/2017 ያካሄደውን 25ኛ ጉባዔ መጠናቀቅ ተከትሎ ረቡዕ ሐምሌ 2/2017 ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል፡፡

በድር ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውሮፓን ጨምሮ 27 የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላትን የሚወክል ድርጅት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular