Homeዜናና ወቅታዊዜናበድር ኢትዮጵያ እና ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ባንድነት ለመሥራት ተስማሙ

በድር ኢትዮጵያ እና ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ባንድነት ለመሥራት ተስማሙ

ዋና መቀመጫቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት በድር ኢትዮጵያ እና ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፤ ባንድነት ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል።

ሁለቱ አንጋፋ የሙስሊሞች ድርጅቶች ባንድነት ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቀው በድር ኢትዮጵያ፣ በካናዳ ከሰኔ 26/2017 እስከ ሰኔ 29/2017 ያካሄደውን 25ኛ ጉባዔ መጠናቀቅ ተከትሎ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 2/2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ድርጅቱ በመግለጫው በካናዳ ቶሮንቶ የተካሄደው ጉባዔ የበድር ኢትዮጵያን ጉዞ የዘከረ ብቻ ሳይሆን ከ11 በፊት “በአነስተኛ አለመግባባት” ከቤተሰቡ ተለይቷል ያለው ፈርስት ሂጅራ “ወደ ቤቱ የተመለሰበት” መሆኑን ገልጿል።

ይኸው መግለጫ በድር ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ችግሩን ለመፍታት የሄደበትን ርቀትና የፈርስት ሂጅራ አመራሮች ወደ ፊት ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሷል።

ባለፉት 11 ዓመታት “ድርጅቶቹን ለማገናኘትና ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ” በወንድሞች፣ እህቶችና አባቶች እንዳሉ ሁሉ ጥቂቶች ደግሞ “ልዩነቱን ለማስፋት ተግተው ሠርተዋል” ያለው መግለጫው፤ ይህ ሁሉ አልፎ “ሁሉንም ወገን ባስደሰተ መልኩ” ስምምነቱ ሊከናወን መቻሉን ያትታል።

ፈርስት ሂጅራ “ወደ ቤቱ መመለሱን አባላት በደስታ ስሜት” እንደተቀበሉት በመግለጽም በሁለቱ ድርጅቶች መራራቅ ምክንያት ሳይሠሩ የቀሩ እና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በአስቸኳይ እንዲከናወኑ እንደሚደረግ አስታውቋል።

አያይዞም ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ላላቸውና ሥማቸው ላልተጠቀሰ ወንድሞች፣ እህቶችና አባቶች ምሥጋና አቅርቧል።

ከበድር ኢትዮጵያ ጋር ባንድነት ለመሥራት መስማማቱ የተገለፀው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን የተመሠረተው እ.አ.አ በ1986 መሆኑን በድረ ገጹ ላይ ያሠፈረው መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ በድር ኢትዮጵያ ባለፈው ሣምንት በቶሮንቶ በሚገኘው ነጃሺ ኢስላማዊ ማዕከል አማካኝነት ጉባዔውን ሲያካሄድ መልካም ምኞት የሚገልጽ መልዕክት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አሠራጭቷል።

በካናዳ የተከናወነውን ዓመታዊ ጉባዔ ያጠናቀቀው በድር ኢትዮጵያ በበኩሉ፤ አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውሮፓን ጨምሮ 27 የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላትን የሚወክል ድርጅት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት 24ኛ ጉባኤ “ኢስላማዊ መርሆች ላይ ፀንቶ መቆም” በሚል መሪ ቃል በአሜሪካ ዳላስ አከናውኗል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ማካሄዱም ይታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular