በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የ12 ቀን ጦርነት” የሚል ሥያሜ የተሰጠው እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በመሰነዘር ያስጀመረችው ጦርነት፤ በተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሏል፡፡ ጦርነቱ በተኩስ አቁም ስምምነት አብቅቷል በሚል በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከመታወጁ በፊት፤ ትናንት ሰኞ ምሽት ኢራን በኳታር ዶሐ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን አል ኡዴይድ የተባለውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር የሚሳኤል ጥቃት ሠንዝራበታለች፡፡ ጥቃቱ ቅዳሜ እለት አሜሪካ በኢራን ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ መሆኑን የቴህራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
ምላሹ የመጣው የሀገሪቷ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ዓብዱልረሂም ሙሳቪ፤ ኢራን ለአሜሪካ ጥቃት “ተመጣጣኝ ምላሽ” እንደምትሰጥ ከዛቱ በኋላ ነው፡፡ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሀገሪቱ “በሉዓላዊነቷ፣ በግዛት አንድነቷ እና በደኅንነቷ” ላይ የተፈፀመባትን ጥቃት “በምንም ዓይነት ሁኔታ ዝም ብላ እንደማትመለከት” በመግለጽ፤ ለትራምፕ እና አጋሮቻቸው “ግልጽ” መልዕክት መተላለፉን መናገራቸውን ተስኒም የተሰኘው ለአብዮታዊ ዘቡ ቅርበት ያለው መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡ ከመኖሪያ ቤቶች ራቅ ብሎ በተሰዘረው ጥቃት በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ኢራን፣ አሜሪካም ሆነ ኳታር ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
የኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት፤ ጥቃቱ ከመኖሪያ አካባቢዎች ርቆ ከመፈፀሙ በተጨማሪ ‘ኳታርን ኢላማ ያደረገ አይደለም’ የሚል ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል፡፡ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የተጋራው መግለጫ፤ “ይህ ድርጊት ወዳጅ እና ወንድም ለሆነው ሀገር ለኳታር እና ለተከበረው ሕዝቧ የሚፈጥረው ምንም ሥጋት የለም፡፡ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከኳታር ጋር ታሪካዊ ግንኙነቶችን ጠብቆ ለማቆየት እና ለመቀጠል ቁርጠኛ ነው” ይላል፡፡
ኢራን ጥቃት የሰነዘረችበት የጦር ሰፈር ወደ ስምንት ሺሕ ገደማ የአሜሪካ ወታደሮች የሰፈሩበት ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ የአየር ኃይል ክፍል ዋና ማዘዣ ሆኖም ያገለግላል፡፡ ኳታር ከ25 ዓመት በፊት አሜሪካ እንድትጠቀምበት የፈቀደችው ይህ የጦር ሰፈር፤ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ ለምታካሄደው ወታደራዊ ተልዕኮ ዋና ማዘዣ እና የአቅርቦት ማዕከል መሆኑንም ስለ ሰፈሩ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የጦር ሰፈሩ አዛዥ አሜሪካ፤ ቅዳሜ እለት ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ የኢራን መልሶ ማጥቃት ከመምጣቱ በፊት አውሮፕላኖችን እና ከባድ መሣሪያዎችን ከአል ኡዴይድ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ማዛወሯን ሚድል ኢስት ዐይ አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን ነግረውኛል ብሎ ዘግቧል፡፡ ይህ ርምጃ አሜሪካ ሳዑዲ ዐረቢያ በኢራን “የጥቃት ዒላማ አትሆንም ብላ በማመኗ” እንዲሁም የጥቃቱን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተደረገ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ እና የዐረብ ባለሥልጣናት ሀገሪቱ አውሮፕላኖችን እና ከባድ መሣሪያዎቹን ማሸሽ የጀመረችው ባለፈው ሣምንት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዘገባው መሠረት የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት በኳታር አሸማጋይነት ስለሚሰነዘረው ጥቃት “ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ” ንግግር አድርገዋል፡፡ ትራምፕም ከጥቃቱ በኋላ የኢራን ባለሥልጣናት ጥቃት ሊሰነዝሩ መሆኑን “አስቀድመው ስለነገሩን ምሥጋና ይገባቸዋል” ማለታቸው ለዚሁ መሆኑን በአሜሪካ ፖለቲካ ሠፊ ሽፋን የሚሠጠው አክሲዮስ የተሰኘው ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ድረ ገጹ የትራምፕ ተኩስ አቁም አዋጅ መመሪያ የተሰጠው ቅዳሜ እለት በቴህራን ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ እንደነበር አስነብቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑኩ ስቲቭ ዊትኮፍን ጠርተው የኢራን ባለሥልጣናት “ለተኩስ አቁም ዝግጁ መሆናቸውን” እንዲያጣሩ ትዕዛዝ በማስተላለፍ፤ ሰውዬውም የተባሉትን ሲያጣሩ በኢራን በኩል “ለተፈጸመብን ጥቃት አጸፋውን ሳንሰጥ ለድርድር አንቀመጥም” የሚል ምላሽ መሰጠቱን አንድ የዋይት ሐውስ ምንጭ አረጋግጠዋል፡፡ ኢራን ኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ጥቃት የሰነዘረችውም ከዚሁ በኋላ ነው፡፡
የኢራን ጥቃት ተከትሎ ከሰዓታት በኋላ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የተኩስ ስምምነት መደረሱን ያወጁት ትራምፕ፤ ጦርነቱ ለዓመታት ሊቀጥል፣ መላውን መካከለኛው ምሥራቅም ሊያጠፋ ይችል እንደነበር በመግለጽ “ነገር ግን አልሆነም፤ መቼም አይሆንምም” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
የኢራን የአጸፋ ጥቃት ሥጋቶችን የማስወገድ ምልክት ተደርጎ መወሰዱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የብሬንት ነዳጅ ዋጋ ከተኩስ አቁሙ በኋላ 5 ነጥብ 7 በመቶ በመውረድ በአንድ በርሜል 71.11 ዶላር እንደተሸጠ የሚድል ኢት ዐይ ዘገባ ያመለክታል፡፡ የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ደግሞ ይህን አሐዝ 7 በመቶ አድርሶታል፡፡ የአሜሪካ የስቶክ ገበያም መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ዘገባው አክሏል፡፡
ዓለም አቀፍ መገናና ብዙኃን ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች መሠረት፤ በኢራን፣ አሜሪካ እና እስራኤል መሃል አሸማጋይ የነበሩት የኳታር አሚር ተሚም አስሳኒ ናቸው፡፡ የተኩስ አቁም ተግባራዊ የሚደረግበትን ሰዓት ጨምሮ የመጨረሻው የተኩስ አቁም ስምምነት ያስፈጸሙት ደግሞ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር በስልክ ሲነጋገሩ ነበሩ የተባሉት የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ቢን ዓብዱረሕማን አስሳኒ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












