Homeዜናና ወቅታዊዜናዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም እና እስራኤልን በወንጀል ተጠያቂ...

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም እና እስራኤልን በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ርምጃዎችን እንዲወስድ እስላማዊ ትብብር ድርጅት ጥሪ አቀረበ

በቱርክ ኢስታንቡል አስቸኳይ ጉባዔ ያደረገው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፤ እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት በማውገዝ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም እና በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ያሳተፈው 51ኛው የድርጅቱ ጉባዔ፤ በእስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕጎችን የጣሰ እንዲሁም የኢራን ሉዓላዊነት ያላከበረ ነው ብሎታል፡፡

በተጨማሪም ኢራን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም እና ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ከሚመለከታቸው የቀጣናው እንዲሁም ዓለም አቀፍ አካላት ጋር በመደበኛነት ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ የሚኒስትሮች ቡድን ማደራጀቱንም አስታውቋል፡፡ አክሎም የጦርነቱ መባባስ በቀጣናው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ መረጋጋት ላይ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

ከእስላማዊ ትብብር ድርጅት 57 አባል ሀገሮች 40 ገደማው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን በመላክ ወደ አንድ ሺሕ ተሳታፊዎች የተገኙበት ጉባዔ የተከፈተው፤ በቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ነበር፡፡ ፊዳን ቀጣናው ከባድ ፈተናዎችን እእየተጋፈጠ በሚገኝበት በዚህ ወቅት “እኛ እንደ ሙስሊም ጠንካራ እና ፍሬያማ ምክክር” አድርገናል ብለዋል። ጉባዔው በማጠናቀቂያው 156 የውሳኔ ሐሳቦችን ያካተተ ስምምነት ማጽደቁንም መናገራቸውን ቱርኪዬ ቱዴይ ዘግቧል፡፡

አያይዘውም ድርጅቱ መስጂደል አቅሷ ላይ መስጂድ ላይ ለተፈፀመ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እ.አ.አ በ1969 መመሥረቱን አስታውሰው፤ ድርጅቱ አሁንም ጭቆናን ለመዋጋትና የፍልስጤማውያንን መብት ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተገናኘ “እስራኤል በአካባቢው ያለውን ግጭት ለማስፋፋት የምትጠቀምበት ስልት በፍልስጤም እየተካሄደ ለሚገኘው የዘር ፍጅት ወንጀል ሽፋን ለመስጠት እንድትጠቀምበት አንፈቅድም” ብለዋል።

በሙስሊም ሀገራት መካከል ያለውን አንድነት በማጉላት የቋጩት ፊዳን፤ የተለያዩ ልዩነቶች ቢኖሩም የጋራ ችግሮችን ለመፍታት አንድነትና ትብብር እንዲኖር አሳስበዋል።

የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ስብሰባ በተጀመረበት ቅዳሜ እለት ንጋት ላይ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ከእስራኤል ጋር በማበር ጥቃት ሰንዝራለች፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “በሁሉም የኒውክሌር ይዞታዎች” ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

አሜሪካ ጥቃቱን የሰነዘረችው እስራኤል ከዐሥር ቀናት በፊት በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ሀገሪቱ በጦርነቱ ላይ ልትሳተፍ ትችላለች የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ መሳተፍ አልያም አለመሳተፏን ለመወሰን የሁለት ሳምንት ጊዜ ያስፈልጋታል ካሉ በኋላ የሐሣብ ለውጥ በማድረግ ነው፡፡

በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ሰፊ ሽፋን እንደሚሰጠው አክሲዮስ ዘገባ ከሆነ ግን ትራምፕ ሁለት ሳምንት መጠበቅ ይኖርብናል ያሉት “ሆን ብለው” ነው፡፡ ዘገባው ሥማቸውን ያልጠቀሳቸው የፕሬዝዳንቱ አማካሪ “ጊዜ ለመግዛት ያደረጉት ነበር” ብለዋል፡፡

አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘውን የሆርሙዝ ሰርጥ እንዲዘጋ የሀገሪቱ ፓርላማ መወሰኑን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የምድር አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የሚያልፍበት መሆኑ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር ባወጣው መረጃ መሠረት፤ በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የሚያልፍበት ሲሆን፣ በዚህም በዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይጓጓዛል፡፡ በባሕር ሰርጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየቶችን በማስከተል የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

በተለይ አሜሪካን ጨምሮ ከገልፍ ሀገሮች በሚገባ የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ በሆኑት በሌሎችም ሀገሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ ኢራን ከመተላለፊያው ጋር በተገናኘ ውሳኔ እንዳታሳልፍ ጫና እንድታደርግ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለቻይና ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክሲዮስ እንደዘገበው ከሆነ፤ ሩብዮ ለቻይና ጥሪ ቢያቀርቡም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን መተላለፊያውን የምትዘጋ ከሆነ “በኢኮኖሚ ረገድ ራስን እንደማጥፋት የሚቆጠር” ውሳኔ ስለሚሆን ማድረግ አለማድረጉ ለረሷ የሚተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ብሬንት የተሰኘው ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል የ5 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ዛሬ ሰኞ 81 ዶላር እንደተሸጠ ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular