Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየእስራኤል ጥቃት፣ እስላማዊ ትብብር ድርጅት እና የነዳጅ ጉዳይ

የእስራኤል ጥቃት፣ እስላማዊ ትብብር ድርጅት እና የነዳጅ ጉዳይ

ባለፈው ሐሙስ ንጋት እስራኤል በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሒሴን ብራሂም ጣሃ ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡ ሒሴን ብራሂም ጣሃ ጥቃቱን ያወገዙት፤ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር መሆኑን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ጣሃ እስራኤል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢራን ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በጣም አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት በ“ጠንካራ” ቃላት ነው፡፡ አያይዘውም የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ባንድነት በእስራኤል የተፈጸመውን ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ለመመከት ድጋፍ ለማሰባሰብ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው፤ የሙስሊም ሀገሮች በቀጣናው ላይ እየጨመረ የመጣውን የእስራኤልን “ሕገ ወጥ [ድርጊት] እና ጥቃት” ለመቋቋም የጋራ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

አክለውም እስራኤል የዓለም አቀፍ ሕግ እና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ የፈጸመችው ግልጽ ጥሰት፣ በአካባቢያዊ እና ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ሥጋት መፍጠሩን በመጥቀስ፤ ጥቃቶች በአሁኑ ሰዓት በሥልጣን ላይ ያለው የእስራኤል አገዛዝ “ተጨማሪ ወንጀሎችንና ጥቃቶችን የሚያበረታታ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው” ብለዋል፡፡

እስራኤል ከባለፈው ሳምንት ጁመአ አንስቶ በኢራን ግዛት ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን በማድረስ የኑክሌር እና የሚሳኤል ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናትን እና ሣይንቲስቶችን መግደሏን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የነዳጅ መሠረተ ልማትም እንዲሁ ዒላማ ተደርጓል። ኢራንም በመላ እስራኤል በርካታ አካባቢዎችን ዒላማ በማድረግ ሚሳኤሎችን በመጠቀም አጸፋውን መስጠቷን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

አምስተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ኢራን የእስራኤል የስለላ ድርጅት ‘ሞሳድ’ ዋና መሥሪያ ቤትን በሚሳኤል መምታቷን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ተስኒም በዛሬው እለት ዘግቧል፡፡ የዜና ወኪሉ የሞሳድ መሥሪያ ቤት በእሳት ተያይዞ የሚያሳዩ ፎቶዎችንም አጋርቷል።

እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ በዚያው እለት የነዳጅ ዋጋ 10 በመቶ ገደማ ጨምሯል፡፡ ብሬንት የተሰኘው ነዳጅ ዋጋ ትናንት ሰኞ በ3 ነጥብ 38 በመቶ ከፍ ብሎ አንድ በርሜል በ71.84 ዶላር ተሸጧል፡፡ ከጥቃቱ በፊት የአንድ በርሜል ብሬንት ዋጋ 69 ዶላር ነበር፡፡

ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ቀድሞ እንደተገመተው ሳይሆን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ባለበት እንዲገታ ያደረገው ዋናው ምክንያት ኢራን በዐረብ ባሕረ ሰላጤ የሚገኙትን በነዳጅ የበለጸጉ ሀገሮችን በቦምብ አለማጥቃቷ ወይም በዓለም ላይ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የባሕር ላይ ነዳጅ የሚያልፍበትንና ኢራንን ከባህረ ሰላጤው ሀገሮች የሚለየው የሆርሙዝ ጠረፍን እንደምትዘጋው ዛቻ ብታሰማም ተግባራዊ አለማድረጓ ነው። እንደ ዘገባው ከሆነ፤ እስራኤል እና ኢራን ለኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ ጥበቃ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት እስራኤል በሣምንቱ መጨረሻ በኢራን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ሁለት የጋዝ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ሰንዝራለች። ኢራን በአጸፋው በሃይፋ የሚገኘውን የእስራኤሉ ባዛን የተሰኘ የነዳጅ ማጣሪያ ሕንጻ ላይ ቦንብ በመጣል ከፍተኛ እሳት እንዲነሳ አድርጋለች።

ጥቃቶቹ ቢቀጥሉም በሁለቱም ወገኖች በኩል ከፍተኛ የአቅርቦት መቋረጥን ለማስቀረት ሲባል “በጥንቃቄ” እየተከናወነ መሆኑን ታዛቢዎችን ዋቢ በማድረግ ዘገባው አስፍሯል፡፡ ጦርነቱ በቀጠለበት በዚህ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለነዳጅ ኢንዱስትሪው ገንዘብ በማቅረብ የሚታወቀው የአሜሪካው ሲቲ ባንክ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ60 እስከ 65 ዶላር እየተሸጠ ሊቀጥል እንደሚችል ትንበያ አስቀምጧል፡፡

ባንኩ ይህን ግምት ቢያስቀምጥም፤ ኢራንን ከባሕረ ሰላጤው አገራት የሚለየው የሆርሙዝ ጠረፍ ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ የመዘጋት እድል የሚኖረው ከሆነ በአሜሪካና አውሮፓ ሸማቾች ላይ ጫናውን ሊያሳርፍ እንደሚችል ባለሞያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ይህ ከተከሰተ አሜሪካ እና አውሮፓ እስራኤል ከጦርነቱ እንድታፈገፍግ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉም መላ ምቶች ተሰንዝረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሆርሙዝ ጠረፍ በጥቃት ከተመታ በጦርነቱ ላይ አሜሪካ ተሳታፊ እንድትሆን የሚጋብዝ መሆኑንም የሚናገሩ አሉ፡፡

ከእስራኤል ጥቃት በኋላ የባሕረ ሰላጤው ሀገሮች ጥቃቱን ቢያወግዙትም ከማንኛውም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን ለማራቅ እየሞከሩ መሆኑን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ ሬውተርስ ዜና ወኪል ሰኞ ዕለት እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ኢራን፤ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ኦማን እና ኳታር ጋር በመሆን ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም እንዲደረግ በትራምፕ አስተዳደር ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቃለች።

ዘገባው ይህን ቢልም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባጋይ፤ የእስራኤል ጥቃት ያለ አሜሪካ አይዞህ ባይነት ሊታሰብ የማይችል መሆኑን በመጥቀስ፤ በሀገሪቱ ላይ ወቀሳ መሰንዘራቸውን ፕረስ ቲቪ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ ጥቃቱን እንድታወግዝ የጠየቁት ቃል አቀባዩ፤ ሀገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት አባል በመሆኗ ግዴታ እንደሚጣልባትም ተናግረዋል፡፡ ይህ ባልተፈጸመበት ሁኔታ የሚደረግ ማንኛውም የተኩስ አቁም ንግግር “ትርጉም የለሽ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች በአሁኑ ሰዓት የዐረብ ሀገሮች ባለሥልጣናት፤ አሜሪካ ከእስራኤል ጎን በመሰለፍ ቴህራን ላይ የቦምብ ጥቃት የመሰንዘር እድሏ እየጨመረ መጥቷል የሚል ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡

በዚህ መሀል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራኗን መዲና ቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው በጦርነቱ ላይ ተጨማሪ ግለት ጨምሯል፡፡

እ.አ.አ በ1980ዎቹ በኢራን – ኢራቅ ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የባሕር ኃይል የኩዌት የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቦችን ለመጠበቅ በሚል ጣልቃ በመግባቱ ከኢራን ጋር በቀጥታ ግጭት ውስጥ መግባቱንም ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular