በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡት አራት ባንኮች እንዲሁም በመስኮት ደረጃ አገልግሎት ሰጪዎች በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ያስመዘገቡት አፈጻጸም መረጃ ወጥቷል፡፡ በዚህም መረጃ መሠረት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከ332 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ሲደርስ፤ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተለቀቀው ፋይናንስ (ብድር) መጠን ደግሞ ከ151 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ለብድር የዋለው የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ58 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡
ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራቱ ባንኮችና አገልግሎቱን በመስኮት ደረጃ እየሰጡ ባሉት ባንኮች በኩል፣ ፋይናንስ ከተደረገው ገንዘብ ውስጥ ብልጫ ያለውን ፋይናንስ ያቀረበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ በዘጠኝ ወራት በሲቢኢ ኑር በኩል ፋይናንስ የተደረገው መጠን 68 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ቀሪው ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሚሰጡ አራት ባንኮችና በመስኮት ደረጃ አገልግሎት በሚሰጡ ባንኮች በኩል የተሰጠ ነው፡፡
በተመሳሳይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባንኮቹ ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በሒሳብ ዓመቱ ዘጠኝ ወራት መጨረሻ ላይ ከ332 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተቀማጭ ገንዘብ ከ109 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም በሲቢኢ ኑር በኩል የተሰባሰበው የገንዘብ መጠን ብልጫ ያለው ነው፡፡ ከወለድ ነፃ ከተሰባሰበው 332 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ውስጥ የባንኩ ድርሻ 172 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
በ2017 የበጀት ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች እየጨመረ በመምጣት በሁሉም ባንኮች ከወለድ ነፃ አስቀማጮች ቁጥር ከ28 ነጥብ 84 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይህ አኃዝ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከአሥር ሚሊዮን በላይ ብልጫ ማሳየቱን የሪፖርተር ጋዜጣ መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 20 ነጥብ 57 ሚሊዮን ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












