Homeዜናና ወቅታዊዜናፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በተያዘው ወር ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና ለመስጠት የያዙትን ዕቅድ...

ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በተያዘው ወር ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና ለመስጠት የያዙትን ዕቅድ አጠፉ

ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በተያዘው ወር ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት የያዙትን ዕቅድ ማጠፋቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ሁለቱ ሀገሮች ዕውቅናውን ይሰጣሉ ተብሎ የነበረው በሳዑዲ ዐረቢያ እና ፈረንሣይ አስተባባሪነት በሚዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ነው፡፡

ቀደም ብለው የወጡ መረጃዎች የዛሬ ሣምንት ተጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው በአሜሪካ ኒውዮርክ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባኤ ላይ፤ ፈረንሣይና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገሮች ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና እንዲሰጡ የማግባባት እንቅስቃሴ ሰታደርግ መቆየቷን ይጠቁማሉ፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ፈረንሣይ ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና የምትሰጠው ጉዳዩ ‘ምክንያታዊ እና ሞራላዊ’ በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፈረንሣይና አጋሮቿ ዕውቅናውን ሲሰጡ በምትኩ አንደኛዋ የጉባዔው አስተባባሪ ሳዑዲ ዐረቢያ ለእስራኤል ተመሳሳይ ወሮታ እንደምትከፍል ማክሮን ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው፤ የፈረንሣይ ባለሥልጣናት ከጉባዔው አስቀድሞ ባለፉት ቀናት ለእስራኤል አቻዎቻቸው ጉባዔው ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት አመቺ እንደማይሆን ነግረዋቸዋል። ሀገሮቹ ከዚህ ይልቅ አሁን ትኩረት የሚያደርጉት ወደ ዕውቅና የሚወስዱ ርምጃዎች ላይ መሥራትን ነው፡፡ እነዚህም በጋዛ ውስጥ ዘላቂ የተኩስ አቁም፣ የምርኮኞች መለቀቅ፣ በማሕሙድ አባስ የሚመራው የፍልስጤምን አስተዳደር ማሻሻል፣ በጋዛ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ድፍ ማድረግ እንዲሁም ሐማስ በከተማዋ ውስጥ ያለው አገዛዝ እንዲያበቃ መሥራት ናቸው፡፡

ስለ ጉዳዩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተናገሩት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮ፤ በጉባዔው ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና መስጠት “ትዕምርታዊ” መሆኑን የገለጹ ቢሆንም ሀገራቸው በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እንደ መሆኗ መጠን “ያለ አጋሮች ድጋፍ ይህን ያለማድረግ የተለየ ኃላፊነት” እንደሚጣልባት አስረድተዋል፡፡ በዚህም ድጋፍ ያልሰጧቸው ሀገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሁን ይህን ቢናገሩም ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን፤ ፈረንሳይ ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት “ከልካይ እንደሌለባት” ተናግረው ነበር፡፡

ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና ባይሰጡም እስካሁን ድረስ 147 የዓለም ሀገሮች ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ በተለይ ፈረንሣይ ባለፉት ወራት ለፍልስጤም ዕውቅና እሰጣለሁ ማለቷ ሌሎች የአህጉሩን ሀገሮች ለማስተባበር አመቺ የነበረ ቢሆንም በፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት የአሜሪካ ጫና ወደ ኋላ እንዲፈገፍጉ ማድረጉም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular