የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በክልሉ ውስጥ በሚገኘው ሐዲያ ዞን በሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚደርሰው ጥቃት እየተባባሰ የማኅበረሱቡን የእምነት ደኅንነት አስጊ ሁኔታ ላይ መድረሱን ገልጿል። ምክር ቤቱ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቋል።
ከፍተኛ ምክር ቤቱ ይህን የገለጸው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 2/2017 ባወጣው መግለጫ ነው። እንደ መግለጫው ከሆነ፣ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ፣ በቅዱስ ቁርኣን እና በመስጅዶች ላይ ትንኮሳው የሚካሔደው በሐዲያ ዞን በአን ሌሞ እና በሌሞ ወረዳዎች ውስጥ ነው።
ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል ከዚህ በፊት በእንሌሞ ወረዳ በጪንጎ ቀበሌ በመስጂድና መኖሪያ ቤት ድረስ በመዝለቅ ከ30 በላይ መስሊሞች ላይ ጥቃት ቢደርስም በወረዳው እና በዞኑ በኩል አንድም ሰው ተጠያቂ ሣይደረግ ተድበስብሶ መታለፉን አስታውሷል።
በወረዳው ምሥራቅ አንሌሞ ቀበሌ በሱመያ መስጅድ እና በአራዕልዶ መስጂድ በሁለቱም መስጅዶች መካከል ርቀቱን ባልጠበቀ መልኩ ቤተክርስቲያን መገንባት በመጀመሩ መብታቸውን ለመጠየቅ አቤቱታ በቀረቡ በሁለቱም መስጂድ ኮሚቴዎች ላይ የውሸት ክስ በማቀነባበር በሰባት ሰዎች ላይ ከአንድ ዓመት በላይ ተፈርዶባቸው ሆሳዕና ማረሚያ ቤት በእስር እንደሚገኙም ጠቅሷል።
በዚሁ ቀበሌ በሚገኝ መስጅድ ላይ ደረሳዎቾ በተገኙበት በማታ መስጅድ ከእነ ቁርኣን እና ኪታቡ ተቃጥሏል ያለው ምክር ቤቱ፣ ለዚህም ጥቃት ለአንሌማ ወረዳ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቤቱታ ቢቀርብም አቤት ባዮችን እንደገና ወንጀለኛ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
በዚህ ድርጊት መነሻ መግለጫ ለማወጣት መገደዱን የገለፀው ምክር ቤቱ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት፣ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱም ከተማ አስተዳዳር መጅሊሶች በዞኑ የሚፈፀመውን የሙስሊሞችን ጥቃት እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአጭር ጊዜ ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል። (ሚንበር ቲቪ)












