በ1446 ዓ.ሂ የተመዘገበው የሑጃጅ ቁጥር በሠላሳ ዓመት (በኮቪድ ወቅት የተመዘገበውን ሳያካትት) አነስተኛው መሆኑን የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር መረጃ አመላከተ። በሚኒስቴሩ መረጃ መሠረት በዘንድሮ ሐጅ የተሣተፉ ምዕመናን ቁጥር 1 ሚሊዮን 673 ሺሕ 230 ነው።
ከነዚህ መካከል 1 ሚሊዮን 506 ሺሕ 576 ከ171 የዓለም የዓለም ሀገሮች የተጓዙ ናቸው። ቀሪዎቹ 166 ሺሕ 654 ምዕመናን ከዚያው ከሳዑዲ ወደ ቅድስቲቱ መካ ከተማ ገብተዋል።
ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ160 ሺሕ ያነሰ ነው። ሚኒስቴር ለቁጥሩ መቀነስ የጠቀሰው ምክንያት ባይኖርም በተለይ በመላው ዓለም የሚስተዋለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ዋንኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ዘገባዎች ጠቁመዋል።
በዚህም ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኙ የአፍሪካ እና የደቡብ እስያ ሀገሮች ዜጎች የኢኮኖሚ መቀዛቀዙ ባስከተለው የዋጋ ግሽበት፣ የመጓጓዣ አገልግሎት ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም ለመስዋዕት የሚቀርቡ እንስሳት ዋጋ ጭማሪ ተጎጂ መሆናቸው ተነግሯል።
በሐጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው የምዕመናን ቁጥር የተመዘገበው ከ15 ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2012 ነበር። በወቅቱ ከመላው ዓለም 23.16 ሚሊዮን ምዕመናን ተሣታፊ ሆነዋል።
በዘንድሮ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከኢትዮጵያ የተጓዙ ምዕመናን ቁጥር 6 ሺሕ 200 መሆኑ ተገልጿል። ይህ ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ከተጓዙት 12 ሺሕ ምዕመናን ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል። ከክፍያ አኳያ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሣተፍ ባለፈው ዓመት ሲከፈል ከነበረው 90 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል።












