እስልምና በመላው ዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ሃይማኖት ነው ሲል የአሜሪካው ፒው የምርምር ማዕከል አሳውቋል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረት ባለፉት 15 ዓመታት፤ 350 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ወደ እስልምና ተመልሰዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በመላው ዓለም ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማጥናት እና የሕዝብ አስተያየት በመሰብሰብ የሥነ ሕዝብ አዝማሚያዎች ላይ መረጃ የሚያወጣው ማዕከሉ፤ አዲሱን የጥናት ውጤት ይፋ ያደረገው ሰኞ እለት ነው፡፡ በጥናቱ ላይ ከእስልምና በተጨማሪ የሌሎች ሃይማኖቶች አዝማሚያዎችም ተካተዋል፡፡
በጥናት ውጤት መሠረት እስልምና ባለፉት ዓመታት በፍጥነት ዕድገት ከማስመዝገቡ ባሻገር፤ ሙስሊሞች ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በአማካይ ንጽጽር ሲቀርቡ በርካታ ልጆች የሚወልዱና በዕድሜ እርከንም ወጣቶች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2020 ድረስ ባሉት አምስት ዓመታት የአንዲት ሙስሊም እናት አማካይ የወሊድ ምጣኔ በንጽጽር ሲቀመጥ 2 ነጥብ 9 ነው፡፡
በቁጥር በርክተው የሚታዩትም ሙስሊሞች በአብላጫነት በሚኖሩባቸው ሀገሮች ውስጥ መሆኑን ጥናቱ ያመለከታል፡፡ ከዓለም ሀገሮች መካከል በካዛክስታን፣ ቤኒን እና ሊባኖስ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቁጥር ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ሲያስመዘግብ፤ በኦማን እና በምሥራቅ አፍሪካዋ ሀገር ታንዛኒያ ደግሞ ቁጥሩ ቀንሷል፡፡
እስልምና በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም ወደ ሁለት ቢሊዮን ገደማ ተከታይ ሕዝብ በመያዝ በሁለተኛው ደረጃ ተቀምጧል፡፡ ባለፉት ዓመታት ወደ እስልምና የተመለሱት በአብዛኛው በአዋቂ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች መሆናቸውን ይፋ ያደረገው ጥናቱ፤ ይህ በንጽጽር ሲታይ ብቸኛው የዓለም ሃይማኖት እንደሚያደርገው ጠቁሟል፡፡
ፒው የምርምር ማዕከል ከእስልምና በተጨማሪ በዓለማችን ሃይማኖት አልባነት እየጨመረ መምጣቱንም በጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝብ ወደ ሁለት ቢሊዮን እንደሚጠጉ የተገመቱት እነዚህ ሃይማኖት አልባ ሰዎች፤ ከ2010 ወዲህ በ270 ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየታቸው ተገልጿል፡፡ የሃይማኖት አልባ ሰዎች ቁጥር ከሙስሊሞች ጎን ለጎን በዓለም ላይ ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ዕድገት ያሳየ ብቸኛው ሆኗል፡፡
ሃይማኖት አልቦ ማንነት በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ከ2010 አንስቶ 97 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። የትኛውንም ሃይማኖት የማይከተሉ በርካታ ሰዎች የሚኖሩት ደግሞ በቻይና ሲሆን፣ ቁጥራቸው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ገደማ ተገምቷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












