በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የምትገኘው ማሌዥያ፤ እ.አ.አ በ2025 የሙስሊሞች ተመራጭ መዳረሻ ሀገር ተብላ ተመርጣለች፡፡ ይህ ይፋ የተደረገው በሲንጋፖር በተካሔደው ‘አራተኛው ሐላል ኢን ትራቭል አዋርድስ’ ላይ ነው፡፡
የዓለም ሙስሊም የጉዞ መረጃ ጠቋሚ ይፋ በተደረገበት በዚህ ሥነ ሥርዐት ላይ፤ ሀገሪቱ የተመረጠችው ለዘጠነኛ ተከታታይ ዓመት ነው፡፡ ሀገሪቱ ለሙስሊሞች ተመራጭ የጉዞ መዳረሻ ተብላ ለመመረጧ፤ የተሟላ የሐላል ምግብ አቅርቦት፣ የመስገጃ ሥፍራዎች እና ለቤተሰብ የተመቸ የመዝናኛ ሥፍራ ማዘጋጀቷ እንዲሁም በአጠቃላይ ለሙስሊሞች የተመቸ ባህል ያቀፈች መሆኗ ተጠቅሷል፡፡

የሙስሊሞች ተመራጭ መዳረሻ ሀገር ተብላ የተመረጠችው ማሌዥያ፤ የሐላል ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ራሱን የቻለ ኮሚሽን ልታቋቁም መሆኑን በቅርቡ ማሳወቋ ይታወቃል፡፡የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፤ ከሀገሪቱ የሐላል ምክር ቤት የኮሚሽን ማቋቋሚያ ምክረ ሐሳብ ቀርቦ በቀጣይ ጉዳዩ ወደ ካቢኔ እንዲመራ ከተደረገ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
በማሌዥያ እ.አ.አ በ2023 በሐላል ኢንዱስትሪ በድምሩ 54 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የወጪ ንግድ ግብይት ተካሄዷል፡፡ ይህ መጠን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ 10 በመቶ የሚገመት ድርሻ ማበረከቱም ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












