የፍልስጤም አውቃፍ እና ሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ የእስራኤል ወታደሮች የመስጂደል አቅሷን መግቢያ በር መቆለፋቸውን ተከትሎ ተቃውሞውን አሰምቷል። ወታደሮቹ የመስጅዱን መግቢያ በሮች የቆለፉት ትናንት ጁመዓ ነው።
የፍልስጤም ዜና አገልግሎት ዋፋ እንደዘገበው፤ ወታደሮቹ በዕለቱ መስጅዱ ላይ ከበባ የፈፀሙት ከፈጅር ሰላት በኋላ ነው። በዚህም ምዕመናን ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ሙከራ ሲያደርጉ መከልከላቸውንም የዓይን እማኞችን ጠቅሷል።
ከቆይታ በኋላ ወደ መስጂደል አቅሷ መዳረሻዎችን ዘግተዋል። ወታደሮቹ የመስጅዱን መግቢያ በር የቆለፉት የእስራኤል ጦር በኢራን ጥቃት በመሰንዘር በወረራ በያዘው ዌስት ባንክ ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ተከትሎ መሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በቁድስ ከተማ በሚገኘው እስላማዊ ወቅፍ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ የዲፕሎማሲ እና ቱሪዝም ዳይሬክተሩ አውን ባዝባዝ ለሚድል ኢስት አይ እንደተናገሩት፤ እስራኤል ከኢራን ጋር የገባችበትን ውዝግብ እንደ ሽፋን በመጠቀም የመስጂደል አቅሷን ቅጽር ግቢ በይበልጥ ለመቆጣጠር እየተጠቀመች ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የወቅፍ ሠራተኞች ብቻ ወደ ግቢው መዝለቅ እንደተፈቀደላቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ለጊዜው ተብሎ ሲዘጋ እንደገና መቼ እንደሚከፈት ዋስትና የሚሰጥ አካል አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም እስራኤል አሁን ያለውን የጦርነት ሁኔታ ተጠቅማ አዳዲስ ገደቦችን በመጣል እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመቀየር ጥረት እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር እንደሌላቸውም አስረድተዋል፡፡
ዓለም በተለይም ደግሞ የሙስሊሙ ዓለም ትኩረቱን በጋዛ እና በኢራን ላይ ባደረገበት ወቅት እስራኤል በመስጅዱ ላይ ያላትን ዕቅድ ቀስ ቀስ እያሳካች ነው በማለትም እየተፈጠረ ነው ያሉትን ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ቀድሞ ለሰነዘረው ጥቃት ኢራን ትናንት ምሽት አፀፋ መስጠቷን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል። (ሚንበር ቲቪ)












