Homeየቲቪ ፕሮግራሞችበአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዳይወስዱ...

በአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዳይወስዱ መደረጉን የሙስሊም ሕግ ባለሞያዎች ማኅበር አወገዘ

የኢትዮጵያ ሙስሊም ሕግ ባለሞያዎች ማኅበር፤ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሃያ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዳይወስዱ መደረጉን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዞታል።

ማኅበሩ ድርጊቱን ያወገዘው ዛሬ እሑድ ሰኔ 8/2017 ለሚንበር ቲቪ በላከው መግለጫ ነው። በመግለጫው ላይ እንደሠፈረው፣ ፈተናው እንዳይወስዱ ክልከላው የተጣለባቸው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በአክሱም ከተማ ውስጥ በሚገኙት ክንደያ እንዲሁም አብርሃ ወ አጽብሃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ናቸው። በዚህም ከሰኔ 2/2017 እስከ ሰኔ 7/2017 ድረስ የተሰጠው የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲያልፋቸው ተገድደዋል።

በተማሪዎቹ ላይ የተፈፀመውን የመብት ጥሰት ያወገዘው ማኅበሩ፣ ለደረሰው የመብት ጥሰት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ማህበሩ አክሎም ባደረገው ክትትል በአክሱም ከተማ ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሚከተሉትን ሀይማኖት መሠረት በማድረግ  እየተፈፀመ የሚገኘው የመብት ጥሰት የሚፈፀምበትን መንገድ እየቀያየረ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን መረዳቱን ገልጿል። በመብት ጥሰቱ ምክንያት ተማሪዎች ለስነ ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን፣ በርካታ ሴት ተማሪዎች መሰደዳቸውን እንዲሁም ያለ እድሜ ለጋብቻ መዳረጋቸውን አብራርቷል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ህጎች ትምህርት ሀይማኖታዊ አመለካከትን መሠረት በማድረግ አድሎ ሊፈፀምበት የማይገባ መሆኑን በማስታወስ፣ መንግሥት አድሏዊ አሠራርን የሚደግፉ የትምህርት ፖሊሲዎች፣ ህጎች እና ተቋማት ላይ ቁጥጥር የማድረግ እና የማስተካከያ ርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም የትግራይ ክልል እና የፌዴራል መንግስት ተቋማት ከዚህ ቀደም በአክሱም ከተማ ውስጥ በሚገኙ በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ፣ በአሉሙናይ ሁለተኛ ደረጃ፣ በቀዳማዊ ሚኒሊክ (ወርዒ) ሁለተኛ ደረጃ እና በአብርሃ እና አጽብሃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ውስጥ የሚማሩ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሚከተሉት ሀይማኖት ምክንያት ትምህርት እንዳይማሩ በተደረገበት ወቅት የማስተካከያ ርምጃ አለመውሰዳቸው ለመብት ጥሰቱ እውቅና የሰጠ እና ለመባባሱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል።

የደረሰውን ጥሰት ማረም እንዲቻሎ መንግስትን ጨምሮ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ውስጥ የሚገኙ የ8ኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና እንዳይፈተኑ የተከለከሉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ ለደረሰው የመብት ጥሰት እርምት በመውሰድ ተማሪዎቹ በድጋሚ ፈተናውን የሚወስዱበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ እና ጥሰቱን በፈፀሙ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የኢትዮጵያ ሙስሊም የህግ ባለሙያዎች ማህበር ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሙስሊም የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር የተመሠረተው የካቲት 2017 ነው። ማኅበሩ በሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ብሔራዊ እና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ህጎችን መሰረት በማድረግ ለመብቶች መከበር፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን ይገልጻል።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular