Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችብስክሌት ጋላቢው እና ጀልባ ቀዛፊዎቹ ሑጃጅ

ብስክሌት ጋላቢው እና ጀልባ ቀዛፊዎቹ ሑጃጅ

ብስክሌት ሲጋልብ የሚታየው ወጣት አነስ አራዚቂ ይባላል፡፡ ከቤልጅየም በመነሳት ብስክሌት የሚጋልበው ሳዑዲ ዐረቢያ ለመድረስ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ሦስት ወራት ገደማ አስቆጠረ፡፡ ጉዞውን የጀመረው የረመዳን ወር በገባ ሰሞን ነበር፡፡ ወደ አሰበው ለመድረስ በርካታ ሀገሮችን ማቆራረጥ ነበረበት፤ በጽናት አደረገው፡፡ በጉዞው ካቆራረጣቸው መካከል ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ እና ቦስኒያ ይጠቀሳሉ፡፡ ዮርዳኖስን ደግሞ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ተሻግሮባታል፡፡ አነስ በብስክሌት ግልቢያ በርካታ ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን ሲያቆራርጥ፤ በመንገዱ ለሚያገኙት ሰላምታ ያቀርብ ነበር፡፡

ጉዞው ግን በሰላምታ እና ሳቅ ብቻ የታጀበ አልነበረም፡፡ ባለፉት ቀናት ሳዑዲ ደርሶ ለአልአኽባሪያ ቲቪ ጋዜጠኞች የተናገረውም ይህንኑ ነው፡፡ ብስክሌት ጋላቢው እንደሚለው፤ በጉዞው ዋንኛው ፈተና የነበረው ባይተዋርነቱ ነበር፤ ቢደክመው “አይዞህ” የሚለው አልነበረም፡፡ በተለያዩ ሀገሮች ያጋጠመው የተለያየ የአየር ጠባይም እንዲሁ ፈተና ሆኖ እስከመጨረሻው ዘልቋል፡፡ ለዚህም ይመስላል፤ ለጣቢያው ጋዜጠኛ መካ መድረስ የሕይወት ዘመን ሕልሜ ቢሆንም መሳካቱን ማመን ተስኖኝ ነበር ያለው፡፡ አሁንም ቢሆን “ከካዕባ ፊት ለመቆም ቸኩያለሁ” ሲል ተደምጧል፡፡

ቤልጅየማዊው በአውሮፓ መንገዶች በብስክሌት የጻፈው ገድል በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ውዳሴ አስገኝቶለታል፡፡ አቀባበል ያደረጉለት አንድ ባለሥልጣን፤ የአነስ ጉዞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ራሱን በድንበር በማጠር ባሕሉም ቢሆን በተለያየ መንገድ ቢበረዝ ሐጅን ከእውነተኛ መንፈሡ መነጠል እንደማይቻል ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ ሰውዬው የሐጅ እውነተኛ መንፈሥ የሚሉት ‘ተጋድሎን፣ ለተነሱለት ዓላማ መውጣት እና መውረድን’ ነው፡፡ አነስ አራዚቂ ቀደም ብለው ከስፔን አንደሉስ እንደ ጥንቱ በፈረስ ጋልበው መካ የደረሱትን እነ ዓብደላ ፌርናንዴዝን በመከተል በሐጅ ልዩ ተጓዦች መዝገብ ሥሙን አስፍሯል፡፡

የዘንድሮ ሐጅ ልዩ ተጓዦች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ የብሪታንያ ፓስፖርት የያዙት ዓብዱል ወሂድ፣ ተውሲፍ አሕመድ፣ ጆዲ ማክሊንቲር፣ ዶዲር ኡዲን እና ጣሂር አኽታርም ናቸው፡፡ የለንደን ነዋሪዎቹ እነ ጣሂር ለሐጅ የተነሱት ኢንግሊሽ ቻናል ከሚባለው የውሃ አካል በሞተር ጀልባ ተሣፍረው ነው፡፡ 7 ሺሕ 400 ኪሎ ሜትር ለሚረዝመው ጉዞ ጀልባ ቀዛፊ ያደረጉት ራሳቸውን ነው፡፡ አስደናቂው ነገር አንዳቸውም ከዚህ ቀደም ጀልባ የመቅዘፍ ልምድ አልነበራቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ከለንደን ተነስተው በርካታ የአውሮፓ እና ሰሜን አፍሪካ የውሃ መሬቶችን ከማቆራረጥ ወደ ኋላ አላሉም፡፡

ስለ ጉዞው ለዐረብ ኒውስ የተናገረው የቡድን አባሉ ዓብዱል ወሂድ፤ ሐጅን በዚህ መንገድ ለመፈጸም መነሻ የሆነን “የእስልምናን ታሪክ ከሀገራችን የባሕር ታሪክ ጋር አዛምደን መመልከታችን ነው” ብሏል፡፡ ጉዞውን ከመጀመራችን በፊት ለስድስት ወራት የቀዛፊነት ሥልጠና መውሰድ አስፈላጊ ስለነበረ ይህን ማድረጋቸውንም ተናግሯል፡፡ በጉዞው ከኢንግሊሽ ቻናል ተነስተው፤ የፈረንሳዩዋን ማርሴይ፤ የሜዲትራንያን ባሕር ደሴቶቹን ኮርሲካ፣ ሳርዲንያ፣ ሲሲሊ እና ክሪት እየቀዘፉ አልፈዋል፡፡ በግብጽ ስዊዝ ካናል ተሻግረው በመጨረሻ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያዋ ጂዳ ከተማ የሚያደርሳቸውን ቀይ ባሕርን አቋርጠዋል፡፡ በዚህ ሁሉ የውሃ መንገድ ሲጓዙ ከሰባ ቀን አለፈ፡፡

አምስቱ የብሪታንያ ዜጎች በዚህ ጉዞ ሒደት ፈታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጣቸውን ለዜና ድረ ገጹ ተናግረዋል፡፡ የቡድኑ ሌላኛው አባል አሕመድ፤ ከተጋፈጧቸው ፈታኝ አጋጣሚዎች መካከል አንደኛው ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ የጋረጠ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አጋጣሚውን ሲናገር፤ “አንድ ቀን በማለዳ በድንገት ጀልባችን ከስር ፍሳሽ ወደ ውስጥ እያሰረገ እንደሆነ ተረዳን፤ በዚህም ደነገጥን፡፡ በመጨረሻ እንደምንም ችግሩን አስተካክለን ብንመለስም ሁኔታው አስደንጋጭ ነበር፡፡ አልሐምዱላህ! አለፈ” ብሏል፡፡ አሳ ነባሪ ም ጉዟቸውን ለሦስት ያክል ጊዜያት በማደናቀፍ ድንጋጤ ፈጥሮ አልፏል፡፡

እነ አሕመድ ለሐጅ ሲጓዙ የደረሱበትንም የደረሰባቸውንም ለተመልካቾች ሲያጋሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በርካታ አድናቂዎች ማፍራት ችለዋል፡፡ “አይዟችሁ፤ በርቱ – እንዳትረቱ” የሚሏቸውን እነዚህን ተከታታዮች ከቃል ማበረታቻ ባሻገር አንድ ውለታ ጠየቁ፡፡ ይህ ውለታ ገንዘብ የማሰባሰብ ነው፡፡ ጀልባ ቀዛፊዎቹ ገንዘቡን የፈለጉት በፍልስጤም፣ ሊባኖስ፣ ፓኪታን፣ ሶሪያ እና በምሥራቅ አፍሪካዋ ሀገር ኡጋንዳ ለሚገኙ ወላጅ አጥ ሕፃናት ለመለገሥ በማሰብ ነው፡፡ ተከታታዮቻቸው አላሳፈሯቸውም፤ 266 ሺሕ ዶላር ማሳካት ቻሉ፡፡ ተጓዦቹ ተጨማሪ ዓላማ አንግበው ስለነበር ለተከታታዮቻቸው ዳዕዋ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ወሒድ ይህን ማድረግ ለምን እንደፈለጉ ሲያስረዳ፤ “የእስልምናንና የሐጅን ውበት ለዓለም ማሳየት እንፈልጋለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

አምስቱ ጀልባ ቀዛፊ ሑጃጅ የባሕር ጉዞ በቀጣይ በዚህ ሣምንት ይቋጫል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ ለአላህ ሱብሐነ ወተዓላ “ለበይክ” እያሉ ከሀገራቸው እንደተነሱት ሁሉ፤ ቅድስቲቱ መካ ደርሰው ከሌሎች ሚሊዮኖች ባንድነት ይህንኑ ለመድገም ጓጉተዋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ሌሎች ቢሊዮን ሙስሊሞችም ተራው እስኪደርሳቸው ጌታቸውን ይለማመናሉ፡፡ የሐጅ ጉዞ እንደተናፈቀ፤ በላጮቹ የዙልሒጃ ቀናትም ከፊት ቆመው አማኞችን እየጠበቁ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular