Homeዜናና ወቅታዊዜናለዘንድሮ ሐጅ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ቅዱሳኑ ከተሞች መድረሳቸውን የሀገሪቱ ሐጅ እና...

ለዘንድሮ ሐጅ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ቅዱሳኑ ከተሞች መድረሳቸውን የሀገሪቱ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር አስታወቀ

የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፤ ከመላው ዓለም ሀገሮች በዘንድሮ ሐጅ ይሳተፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ምዕመናን መካከል ከከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወደ ቅዱሳኑ ከተሞች መካ እና መዲና መድረሳቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ፤ እስከ ባለፈው እሑድ ድረስ ሳዑዲ የደረሱ ምዕመናን ቁጥር 554 ሺሕ 579 ነው፡፡ እነዚህ ምዕመናን በአየር፣ በባሕር እና በየብስ ተጉዘው የደረሱ ናቸው፡፡

ከተጠቀሰው ቁጥር 538 ሺሕ 766 ሳዑዲ የገቡት በአውሮፕላን ተሳፍረው የደረሱ ሲሆን፣ 14 ሺሕ 391 በየብስ እንዲሁም ቀሪዎቹ 1 ሺሕ 422 በመርከብ የባሕር ላይ ጉዞ አድርገዋል፡፡ በባሕር ተሳፍረው የደረሱት ሱዳናውያን ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሐጅ ሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ስድስት ሺሕ ምዕመናን ምዝገባ ማከናወናቸውን ባለፈው ሣምንት ግንቦት 6/2017 የመጀመሪያዎቹን 448 ሑጃጅ የሸኘው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

“ሚንበር ቲቪ” በክንውኑ ላይ ለመሳተፍ እስካሁን ድረስ ሳዑዲ ዐረቢያ የገቡ ምዕመናንን ቁጥር ለማጣራት የጠቅላይ ምክር ቤቱን ሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድን ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ ምላሽ ባለመስጠታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ ተጓዦችን መቀበል ከጀመረች ሦስተኛ ሣምንት ተቆጥሯል፡፡ በዘንድሮ ዓመት ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከመላው ዓለም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular