የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአስመጪዎች የቅድመ ክፍያ (አድቫንስ ፐይመንት) ቀድሞ ከነበረበት አምስት ሺሕ ከፍ በማድረግ ወደ ሐምሳ ሺሕ ከፍ እንዲል ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በጥሬ ገንዘብ የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ በተመሳሳይ ጭማሪ አድርጓል፡፡
ብሔራዊ ባንክ የአስመጪዎች የቅድመ ክፍያ መጠን ወደ ሐምሳ ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ከፍ መደረጉን ያስታወቀው በዛሬው እለት ነው፡፡ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ውሳኔው የተላለፈው “የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓትን በይበልጥ ለማሻሻል” መሆኑን ገልጿል፡፡
የማሻሻያ ርምጃው “ከአቻ ሀገራት ተሞክሮ በመነሣትና ለብዙ ዓመታት ለውጥ ሳይደረግበት የቆየውን አሠራር የመለወጥን አስፈላጊነት በመገንዘብ” የተደረገ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ባንኩ በዛሬው እለት ውሳኔ ያሳለፈበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ለውጭ ሀገር ተጓዦች የሚፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ነው፡፡ እንደ ባንኩ ከሆነ፤ ለውጭ ሀገር ተጓዦች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በጥሬ ገንዘብ የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ በአዲሱ ገደብ መሠረት ለግል ተጓዦች የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ወደ 10 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም ለንግድ ሥራ መንገደኞች ደግሞ 15 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
ይህን የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ወይም በካርድ መውሰድ እንደሚቻል በመግለጽ፤ የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ግለሰቦች ከሒሳባቸው ላይ በካርድ መጠቀም የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉን አመልክቷል፡፡
ማዕከላዊ ባንኩ ከባለፈው ሐምሌ ወር 2016 አንስቶ አዲስ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












