የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሚመርጣቸው ሠላሳ ተወካዮች የሚሳተፉበት በፌደራል ደረጃ የሚደረገው ሀገራዊ የምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ፤ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚካሔድ ታውቋል፡፡ በምክክሩ ላይ ሙስሊሙን የሚወክሉ ተሳታፊዎች ከወጣቶች፣ ሴቶች፣ ከዑለማ እና ምሑራን ተመርጠው ሥልጠና እንደሚወስዱ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የምክክር አስተባባሪ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠቅላይ ምክር ቤቱን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማት የሚሳተፉበት በፌደራል ደረጃ ካሉ የባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰቢያ መድረክ፤ በቀጣይ ሣምንት እንደሚካሄድ ይፋ ያደረገው በዛሬው እለት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው የፌደራል ተቋማትና ማኅበራት የምክክር ምዕራፍን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ገለፃ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተናገሩት የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፤ የፌደራል ተቋማትና ማኅበራት የምክክር ምዕራፍ የሚካሔደው በቀጣይ ሣምንት ጁመዐ ግንቦት 22/2017 መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሒሩት እንዳሉት በአዲስ አበባው የሚሊኒየም አዳራሽ የሚዘጋጀው መድረክ ለሦስት ቀናት ቆይቶ የሚጠናቀቀው ግንቦት 24/2017 ነው፡፡
በመድረኩ ላይ 38 ገደማ ተቋማት እና ማኅበራትን የሚወከሉ ከ800 በላይ ወኪሎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሃይማኖት ተቋማት እንደሚገኙበት የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የአሠራር ሥርዐት መሠረት ለእነዚህ ተሳታፊዎች ጥሪዎችን በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በመድረኩ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ እንደቀረበለት በሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አጀንዳ አንደኛው አስተባባሪ ሐጂ ኑረዲን ጀማል ለ“ሚንበር ቲቪ” አረጋግጠዋል፡፡ ሠላሳ ተወካዮችን የሚያቅፈው የተሳታፊዎች ስብጥር፤ ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከዑለማ እና ምሁራን የሚመረጥ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሥልጠናው የሚሰጥበት ትክለኛ ቀን ላይ ውሳኔ አለመተላለፉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ሲያሰባስብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለምክክር ሒደት የሚቀርቡ የሀገሪቱን ሙስሊሞች አጀንዳዎች ለምክክር ኮሚሽን ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡
መጅሊስ ያቀረባቸው ዘጠኝ አጀንዳዎች ታሪክና ትርክት፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶች፣ የሲቪል መብቶችና ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፣ የሕዳጣን (Minority) መብት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ለሙስሊም ጠልነት ዕውቅና መስጠት እና ማስተካከል፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚና ፋይናንስ ማስፈን የሚሉት ናቸው። (ሚንበር ቲቪ)












