ኢንዶኔዥያዊው ሐጅ ሌጊማን ቤታቸውን የሚመሩት በፅዳት ሠራተኝነት በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ እንደ አብዛኛው ሙስሊም ‘ቢሞላልኝ ሐጅ ማድረግ እፈልጋለሁ’ የሚል ምኞት ታቅፈው ኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምኞት ብቻ ታቅፈው አልተቀመጡም፡፡ ለዚህ እንዲያግዘኝ በሚል ከአርባ ዓመት በፊት ገንዘብ መቆጠብ ጀመሩ፡፡ ጊዜውን መለስ ብለው ሲያስታውሱት እ.አ.አ 1986 መሆኑ ነው፡፡ ታሪካቸውን ላጫወቱት የገልፍ ኒውስ ጋዜጠኛ፤ “ያን ጊዜ ቁጠባውን የጀመርኩት ባለቤቴ ስላበረታታችኝ ነው” ብለዋል፡፡
በመሐል ቁጠባውን የሚያስተጓጉል ነገር ባይጠፋም፤ “በርትተን ለመቆጠብ ሞክረናል” ያሉት አንደኔዥያዊው፤ ተስፋ ባለመቁረጥ በመጨረሻ ያሰቡት ሞልቶ በዘንድሮ ዓመት ሐጅ ለመሳተፍ ምዝገባ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባል ከአርባ ዓመት በኋላ ውጥናቸው ሲሰምር፤ ለተናፋቂው ጉዞ የተነሱት ብቻቸውን አይደለም፤ “አይዞህ፤ በርታ” ያሏቸውን ሚስታቸውን አስከትለው ከሰሞኑ ሳዑዲ ዐረቢያ ገብተዋል፡፡
ሳዑዲ ከደረሱ በኋላ ሲናገሩ፡- “ደስታው ሊገድለኝ ነው፡፡ ካዕባን ፊት ለፊት ዐየዋለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ አልሐምዱሊላህ! ለዚህ በቃሁ” ብለዋል፡፡

በዓለም ከፍተኛ የሙስሊሞች ቁጥር ባለባት የሐጅ ሌጊማን ሀገር ኢንዶኔዥያ፤ በዘንድሮ ዓመት 221 ሺሕ ምዕመናን በሐጅ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል፡፡
በዘንድሮ ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች የተነሱ ምዕመናን ሳዑዲ ዐረቢያ መግባት ከጀመሩ ሦስተኛ ሣምንት አልፏል፡፡
ከኢትዮጵያ በክንውኑ ላይ ለመሳተፍ ስድስተ ሺሕ ምዕመናን ተመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያውን ጉዞውን የሚያደርጉት በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሳዑዲ ዐረቢያው “ሳዑዲያ” አየር መንገድ ነው፡፡ ከአየር መንገዶቹ መካከል በአራት ሺሕ ሑጃጅ የሚያሳፍረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚሆን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላ ምክር ቤት ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












