በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በፉሪ ክፍለ ከተማ ለሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት የሚውል አምስት ሺሕ ካሬ መሬት ርክክብ ማካሔዱን ያስታወቀው በዛሬው እለት ነው። ምክር ቤቱ የዋና መሥሪያ ቤቱን ግንባታ ከሚያካሄድበት መሬት በተጨማሪ ለዘጠኝ መስጂዶች ግንባታ ቦታ መረከቡን ኃላፊዎች ገልፀዋል።
የሸገር ከተማ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 11/2017 በጽሕፈት ቤቱ በተሰጠ መግለጫ ላይ ነው። በመግለጫው ላይ ከፍተኛ ምክር ቤቱ የመሬቶቹን ርክክብ ያከናወነው ባለፈው ሣምንት ግንቦት 6/2017 መሆኑንም ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት ምክር ቤቱ አከናውኛለሁ ያላቸው ጉዳዮች በኃላፊዎች በተዘረዘረበት መግለጫ ላይ፣ የዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ ይካሄድበታል በተባለበት ፉሪ ክፍለ ከተማ ለሁለት መስጂዶች ግንባታ የሚውል ተጨማሪ መሬት ርክክብ መደረጉ ተገልጿል። የቀሪዎቹ መስጂዶች መሬት በኮዬ ፈጬ፣ ለገጣፎ እና ገላን ክፍለ ከተሞች ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የዘጠኝ መስጂዶች ግንባታ መሬት ርክክብ ተደርጓል በተባለበት ሸገር ከተማ፣ በ2015 አጋማሽ ቢያንስ 19 መስጂዶች ሕገ ወጥ ተብለው መፍረሳቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ገልጾ ነበር። የመስጂዶቹን መፍረስ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ በተነሳ ተቃውሞ የምዕመናን ሕይወት ተቀጥፏል። የምዕመናን ሕይወት የተቀጠፈው ግንቦት 18/2015 ከጁምዓ ሰላት በኋላ ነበር።
የሸገር ከተማ ተረክቤያለሁ ያለውን የመስጂድ መሬት ቀድሞ ከፈረሱት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝነቱን በተመለከተ ሚንበር ቲቪ ለኃላፊዎች ጥያቄ አቅርቧል። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የከፍተኛ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች፣ አሁን የተረከቡት የመሬት ይዞታ ከቀድሞው የበለጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዛሬው መግለጫ ርክክብ ከተደረገባቸው ውጪ አንድ ታላቅ ኢስላማዊ ማዕከል የሚገነባበትን መሬት ጨምሮ በሁሉም የክፍለ ከተማዎች መስጂድ የሚገነባበትን ቦታ ለማግኘት ጥያቄ በማቅረብ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። በዛሬው መግለጫ የመሬት ርክክብ ተደርጎባቸዋል የተባለ መስጂዶቹን ቀጣይ ግንባታ በተመለከተ የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያ የለም። (ሚንበር ቲቪ)
★ ★ ★
Minber TV | EthioSat | 11545 | H | 45000












