Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢትዮጵያ እናት እና ልጅ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ መያዛቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በኢትዮጵያ እናት እና ልጅ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ መያዛቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

ጤና ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ በህመሙ መያዛቸው ከተጠረጠሩ ታማሚዎች በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አማካኝነት በተወሰደው ናሙና በዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ቫይረስ የተያዘ ሰው ማግኘቱን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት ጋር ዛሬ እሑድ ግንቦት 17/2017 በሰጡት የጋራ መግለጫ እንደገለፀው፤ ቫይረሱ እንደተገኘበት የተረጋገጠው የ21 ቀን እድሜ ያለው ሕፃን ልጅ ሲሆን እናቱም በተደረገው ቀጣይ ምርመራ ለቫይረሱ እንደተጋለጠች ለማረጋገጥ ተችሏል። የሕፃኑ አባትም ወደ ጎረቤት ሀገር ሄዶ የነበረ መሆኑ መታወቁና የሄደባቸውን አካባቢዎች እንዲሁም ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችን የመለየትና ክትትል የማድረግ ሥራ ተጀምሯል።

ታማሚው ሕፃን እና እናቱ፣ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ፣ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል አልገጠማቸውም ሲል አሳውቋል።

ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ቫይረሱ ካለባቸው ግለሰቦች ጋር ንክኪ ያለው ሰው ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ ድካም እና የጀርባ ህመም ሲያስተውል በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን የምርመራና ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ አንዲሁም የግል እና የእጅ ንፅህና በመጠበቅና ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ባሉባቸው ታማሚዎች አካባቢ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን በመጠቀም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት ይህ በሽታ በተወሰነ ቦታ ብቻ የታየ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ሳይደናገጥ የተለመደውን አኗኗር መቀጠል እንደሚችል ገልጿል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular